በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለአፍሪካ 20 ሚሊዮን የክትባት መድሃኒት ተጠየቀ


የዓለም ጤና ድርጅት፣ በአፍሪካ፣ የመጀመሪያውን የኮቪድ 19 ከትባት የወሰዱ ሰዎች፣ የሁለተኛውን ዙር እንዲያገኙ፣ 20 ሚሊዮን የክትባት መድሃኒት ጠይቋል፡፡

የጤና ድርጅቱ በአፍሪካ የኮቪድ 19 ቫይረስ ሰርጭት ወረርሽኝ ለሶስት ሳምንታት ያህል ቀንሶ የነበረ መሆኑን ገልጾ፣ አሁን ግን ተመልሶ የመጨመር አዝማሚያ እያሰየ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በቅርብ የተመዘገበው የቫይረሱ ተጋላጮች ቁጥር 4.7 ሚሊዮን መሆኑ የተመለከተ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 128ሺ000 ሰዎች ሞተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ውስጥም የተጋላጮች ቁጥር በ17 ከመቶ ማሻቀቡም ተነግሯል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ድሬክተር ማትሺድሶ ሞኤቲ ፣ ጉዳዩ እጅግ ያሳሳባቸው መሆኑን ቢገልጹም፣ ይሁን እንጂ አፍሪካ ወደ ሶስተኛው ዙር ወረርሽኝ እየገባች ነው ለማለት ጊዜው ገና መሆኑን እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፦

“አፍሪካ ተመልሳ ወደ ወረርሽኙ ከፍተኛ ደረጃ እየገባች ነው ለማለት ጊዜው ገና ነው፡፡ ይሁን እንጂ ባንዳንድ አገሮች ቁጥሩ መጨመሩን እያየን ሲሆን ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተልን ነው፡፡ በሁለት የስለት ቢላዋ ጠርዝ ላይ እየተራመድን መሆኑ ይሰማናል፡፡ ስለሆነም ይህ፣ የኮቪድ 19 ክትባትን በአፋጣኝ መስጠቱን አስፈላጊ ያደርገዋል፡፡”

ድሬክተሯ ሞኤቲ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ወደ 65ሺ ከሚደርሰው አዲሱ የተጋላጮች ቁጥር ውስጥ፣ አንድ ሶስተኛውን ድርሻ ትወስዳለች ይላሉ፡፡

በደቡብ አፍሪካ እየተሰራጨ ያለው አዲሱ የቫይረሱ ዝርያም፣ ወደ ጎረቤት አገራት አካባቢ እየተዛመተ ሊሆን እንደሚችልም ይሰጋሉ፡፡ ለዚህም ናምቢያና ዛምቢያ የቫይረሱ ተጋላጮች ከጨመረባቸው 11 አገሮች መካከል የሚገኙ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

ለአፍሪካ 20 ሚሊዮን የክትባት መድሃኒት ተጠየቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:27 0:00

1.4 ቢሊዮን ህዝብ በሚኖርባት አፍሪካ፣ እስካሁን 28 ሚሊዮን የሚሆኑ የኮቪድ 19 ከትባቶች እንዲዳረሱ ተደርገዋል፡፡ ሞኤቲ እንደሚሉት እስከ ሀምሌ ወር አጋማሽ አፍሪካ የመጀመሪያውን ክትባት ለወሰዱት ሁሉ የሚሰጥ የሁለተኛው ዙር፣ 20 ሚሊዮን የአስትራዜኒካ የክትባት መድሃኒቶች ያስፈልጓታል፡፡ ይህንኑም ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦

“አፍሪካ አሁን ክትባት ያስፈልጋታል፡፡ የክትባቱ ዘመቻ ሂደት ለአፍታም ቢሆን ከተገታ የሰዎችን ህይወትና ተስፋ ወደ ማጣት እናመራለን፡፡ አፍሪካ 10 ከመቶ የሚሆነው ህዝቧን ለማስከተብ እስከ እዚህ ዓመት መስከረም ወር ድረስ፣ 200 ሚሊዮን የክትባት መድሃኒት ያስፈልጋታል፡፡”

ድሬክተሯ በወረርሽኙ የተጋለጡ ሰዎቻቸውን አስከትበው፣ የተትረፈረፈ የክትባት መድሃኒቶች ያላቸው የበለጸጉ አገራት፣ ክትባቶቹን ለአፍሪካ እንዲያካፍሉ ጠይቀዋል፡፡

በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ክትባቶችን ለአፍሪካ ቀድማ የለገሰቸው አገር ፈረንሳይ መሆኗንም ድሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት 100 ሚሊዮን ክትባቶችን ገቢያቸው ዝቅተኛ ለሆኑ አገሮች እንደሚሰጥ ቃል የገባ ሲሆን፣ አሜሪካም በተመሳሳይ 80 ሚሊዮን የክትባት መድሃኒቶችን ለመስጠት ቃል መግባቷን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡

(የቪኦኤ ዘጋቢ ሊዛ ሽላይን ከጄኔቭ ከላከችው ዘገባ የተወሰደ፡፡)

XS
SM
MD
LG