በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኮቪድ-19 እና ክትባቱ


ፎት ፋይል
ፎት ፋይል

በዓለም ደረጃ በኮቪድ-19 የሞቱት ሰዎች ቁጥር፣ ከ900,000 በላይ ደርሷል። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ዋናው የተላላፊ በሽታዎች ጠቢብ፣ የመድሃኒት አምራች የሆነው አስትራዘኒካ ኩባንያ፣ ለቫይረሱ የክትብት ማድሃኒት ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት፣ የሙከራ ሂደቱን ማቆሙ፣ ለመድሃኒቱ አስተማማኝነትና ውጤታማነት የተሰጠውን ክብደት ያመለክታል ብለዋል።

“የሙከራው ሂደት በተለያዩ የክትባቱ መድሃኒት ደርጃዎች የሚደረገው፣ አስተማማኝነቱንና ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ ሲባል መሆኑን መረዳቱ አስፈልጊ ነው” ሲሉ፣ ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ ትናንት አስገንዝበዋል። ፋውቺ የዩናይትድ ስቴትስ ብሄራዊ የአለርጂና የተላላፊ በሽታዎች ተቋም ኃላፊ ናቸው።

ግዙፉ የብሪታንያና የስዊድን የመድሃኒት አምራች ኩባንያው፣ የመድሃኒቱን ሙከራ ለጊዜው ያቆመው፣ በፈቃደኝነት የክትባቱ መድሃኒት የተሰጣት ሴት በመታመምዋ ነው። የክትባቱን መድሃኒት ሙከራ ያቆመው፣ ገና በሚገባ ማጥናት ስላለበት ነው ብለዋል፣ ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸው ፋውቺ።

በሙክራ ወቅት በሚገባ ለመርዳት ያልተቻለ ህመም ሲከሰት፣ የሙከራውን ጥረት ቆም ማድረግ፣ የተለመደ አሰራር ነው ምክንያቱም የሙከራውን ተአማኒነት ለማረጋገጥ ሲባል፣ ምርመራ ማካሄድ አስፋላጊ በመሆኑ ነው ይላል፤ ኩባንያው ያወጣው መግለጫ።

አስትራዘኒካ በሙከራ ላይ ያለውን ክትባት የሰራው፣ ከብሪታንያው ዩኒቨርሲቲ ኦክስፎርድ ጋር በመተባበር ነው። የኮቪድ-19 ክትባት እንዲሆን እየተሰራበት ያለው መድሃኒት፣ ዩናይትድ ስቴትስን፣ ብሪታንያን፣ ደቡብ አፍሪካንና ህንድን ባካተቱ በርካታ ሀገሮች፣ ሰፊ የሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ሙከራ እየተደረገበት መሆኑ የሚታወቅ ነው።

ኩባንያው ስለተከሰተው በሽታ ዓይነት አልተናገረም። ‘The New York Time’ ጋዜጣ በዘገበው መሰረት ግን፣ መድሃኒቱ እንዲሞከርባት የፈቀደችው ሴት፣ ብሪታንያ የምትገኝ ሲሆን፣ ብዙውን ጊዜ ለቫይረስ በመጋለጥ ሊገጥም የሚችል፣ የአከርካሪ አጥንት ምርቀዛ ደርሶባታል። ነገር ግን የታመመችው በክትባቱ ምክንያት ይሁን በሌላ፣ ገና እንዳልታወቀ ጋዜጣው መጠቆሙ አልቀረም።

አስትራዘኒካ የክትባቱን መድሃኒት ሙከራ፣ ለጊዜው እንደሚያዎም ከመግለጹ በፊት፣ ከሌሎች ስምንት የመድሀኒት አምራች ኩባንያዎች ጋር በመሆን፣ አንድ የክትባት መድሃኒት አስትማምኝነቱና ውጤታማነቱ ከመራጋገጡ በፊት፣ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ተቆጣጣሪዎች እንዲያፀድቁላቸው ላለመጠየቅ ቃል ገብተዋል።

የክትባቱ መድሃኒት እንዲጸድቅ ወይም ደግሞ፣ ለአስቸኳይ ሁኔታ እጥቅም ላይ እንዲውል፣ የማጽደቅ ማመልከቻ የሚያቀርቡት፣ አስተማማኝነቱና ውጤታማነቱ፣ በሦስተኛ ደረጃ ሙከራ በኩል ካለፈ በኋላ እንዲሁም፣

የዩናይትድ ስቴትስ የምግብና የመድሃኒት ጠቢንንም የሚገኙባቸው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣኖች፣ ካጠኑት በኋላ ብቻ መሆኑን፣ የዘጠኙ ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስኪያጆች አስታውቀዋል።

ምን ጊዜም ቢሆን ቅድሚያ የምንሰጠው፣ ለሚከተቡት ግለሰቦች ደኅንነት ነው ሲሉ፣ ከፍተኛ ሥራ አስኪያጆቹ አስገንዝበዋል።

ኩባንያዎቹ ባልተለመደ መልክ እንዲህ አይነት ቃል የገቡት፣ በፍጥነት የክትባት መድሃኒት እንዲቀርብ፣ በኩባንያዎች ላይ የፖለቲካ ጫና እየተደረገ ነው የሚል ሥጋት ስላለ መሆኑ ተገልጿል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረሞፕ፣ በህዳር ወር መጀመርያ ላይ የሚደረገው፣ የአሜርካ ምርጫ ከመድረሱ በፊት፣ የኮቪድ-19 ክትባት ሊገኝ ይችላል ሲሉ፣ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል።

XS
SM
MD
LG