በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ተመድ ትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ


ፎቶ ፋይል፦ መቀሌ
ፎቶ ፋይል፦ መቀሌ

በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ አሁንም አስከፊ መሆኑን በትናንት ዕለታዊ ገለጻቸው ያመለከቱት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዲጃሪች አሁንም ለብዙ መቶ ሽህ የክልሉ ነዋሪዎች እርዳታ እየደረሰ እንዳልሆነ ተናገሩ።

በተለይም ሁለት ሶስተኛው የክልሉ ህዝብ በሚኖርበት በገጠራማው አካባቢ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ የኤሌክትሪክ፣ የመገናኛን ጨምሮ አብዛኛው መሰረታዊ አገልግሎት እንደተቋረጠ ነው ብለዋል።

ባንኮችም ከዋና ከተማዋ ከመቀሌ በስተቀር እንደተዘጉ ናቸው ያሉት ቃል አቀባዩ ይህም የእርዳታ ድርጅቶች እና ሌሎችም መሰረታዊ አገልግሎት ለማድረስ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ያደናቅፋል ነው ያሉት።

ውጊያው ሰብል መሰብሰቢያ ወቅት ላይ በመቀስቀሱ ገበያ ላይ የምግብ እጥረት እንደሚታይ ተገልጿል ያሉት ዱጃሪች በዓለም የጤና ድርጅት እምነት በክልሉ ካሉት ሆስፒታሎች ሰማኒያ ከመቶው ከአገልግሎት ውጭ ናቸው ሲሉ አክለዋል።

የግጭቱ መቀጠል ከአስተዳደራዊ ቢሮክራሲው ጋር ተዳምሮ ለችግረኞች የእርዳታ ተደራሽነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት አዳጋች አድርጎታል ሲሉ እርዳታ ያለእንቅፋት መድረስ እንዲችል ለችግረኞችም ጥበቃ የሚሰጥበት አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ መማጸናችንን እንቀጥላለን።

አያይዘውም በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የድርጅቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ችግሩ ሊባባስ እንደሚችል ከሚረዱት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በትግራይ ክልል ባሁኑ ወቅት በመንግሥት እና አጋር ድርጅቶች አማካይነት ለሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዜጎች እርዳታ እየተሰጠ መሆኑን መናገራቸው እና በክልሉ አብዛኛው ክፍል በአሁኑ ጊዜ ለእርዳታ ተደራሽ መሆኑን ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG