በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኮቪድ-19 በዓለም ዙሪያ


በዓለም ዙሪያ በኮቪድ-19 ምክንያት ህይወታቸውን ያጡት ሰዎች ቁጥር ከአራት መቶ ሦስት ሺህ በቫይረሱ የተጠቁት ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከሰባት ሚሊዮን ማለፉን የዩናይትድ ስቴትሱ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ አመልክቷል።

በቫይረሱ በተያዙ እና በሞቱት ሰዎች ብዛት ከዓለም ትልቁን አሃዝ የያዘችው ዩናይትድ ስቴትስ በአሁኑ ወቅት በተጠቂዎቹ ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን፤ ለህልፈት የተዳረጉት ከአንድ መቶ አስር ሺህ መብለጡን የሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲው መረጃ ይጠቁማል።

በኮቪድ-19 ሳቢያ በሞቱት ሰዎች ቁጥር ብዛት ብሪታንያ ብራዚልና ጣሊያን ዩናይትድ ስቴትስን ይከተላሉ፤ በቫይርሱ ተጠቂዎች ቁጥር ደግሞ ብራዚል በሁለተኝነት ከዚያም ሩስያ እና ብሪታኒያ ተመዝግበዋል።

በዓለምቀፉ ወረርሽኝ ይዞታ ከኒውዚላንድ መልካም ዜና ተነግሯል፤ ሀገራቸው የኮቪድ-19ን ስርጭት መግታቷን ጠቅላይ ሚኒስትሩዋ ጃሲንዳ አደርን በዛሬው እለት አስታወቀዋል።

ኒውዚላንድ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ካጸናቻቸው የእንቅስቃሴ እገዳዎች እስካሁን ያልተነሱት እንዲነሱ ወስናለች፤ ድንበሮቹዋ ግን እንደተዘጉ ይቆያሉ።

ይህ በዚህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት የጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድን በፖሊስ እጅ እንዳለ መሞቱን ተከትሎ ከአንድ ሳምንት በላይ በቀጠለው የተቃውሞ ሰልፍ የተሳተፉ ሰዎች ለቫይረሱ ተጋልጠው እንደሆን እንዲመረመሩ እያሳሰቡ ናቸው።

የኒው ዮርኩ አገረ ገዢ አንድሩው ኮሞ ክፍለ ግዛታቸው አስራ አምስት ተጨማሪ የምርመራ ጣቢያዎች እየከፈተ መሆኑን አስታውቀው ተመርመሩ ብለዋል፤

የአትላንታ የሲያትል እንዲሁም የሳንፍራንሲስኮ ክፍለ ግዛቶችና ከተሞች ባለሥልጣናትም ተመሳሳይ ጥሪ አሰምተዋል።

በዛሬ ሰኞ ኒው ዮርክ ከተማ የተዘጉ እንቅስቃሴዎች የሚከፈቱበት የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ ላይ ስታውል፣ ቁጥሩ ወደ አራት መቶ ሺህ የሚገመት ሰራተኛ ሥራ ይጀምራል ተብሎ ተጠብቋል፤ ብዙዎቹ ነዋሪዎች ከሦስት ወር ገደማ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በከተማዋ ባቡሮች ይሳፈራሉ፤

የኒው ዮርክ የግንባታ የፋብሪካ ሰራተኞች የጅምላ ሸቀጥ መደብሮችና አንዳንድ የችርቻሮ ሱቆች ሰራተኞች ወደሥራቸው ይመለሳሉ፣ የከተማይቱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ምግብ ቤቶች ቢያንስ እስከዚህ የአውሮፓ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ ተዘግተው እንደሚቆዩ ተገልጿል።

በፍሎሪዳ ክፍለ ግዛት ደግሞ ትናንት እሁድ ተጨማሪ 1180 የኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን የክፍለ ግዛቱዋ የጤና ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

XS
SM
MD
LG