ዋሺንግተን ዲሲ —
የዩናይትድ ስቴትስ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እጋፈጥበታለሁ ያሉትን የ1.9 ትሪሊዬን ዶላር የኮሮናቫይረስ ምላሽ ዕቅዳቸውን ትናንት ምሽት ላይ አሳውቀዋል።
“በዚህ ወረርሽኝ ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ደሞወዛቸው በመቋረጡ ምክንያት የስብ ዕናና የግል ክብራቸውን ያለፍቃዳቸውና ያለፍላጎታቸው እንዲያጡ ተገድደዋል” ብለዋል ባይደን ለአደጋ ደራሽ ያሉትን ዕቅዳቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት።
ተመራጩ ፕሬዚዳንት ለአብዛኞቹ አሜሪካዊያን የ14መቶ ዶላር ክፍያ በቀጥታ እንዲላክ፣ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ብሄራዊው የክትባት መርኃግብር እንዲጠናከር ለማድረግ እንደሚሠሩ ተናግረዋል። እስከመጭው መስከረምም በየሣምንቱ የ4መቶ ዶላር ክፍያ ሥራቸውን ላጡ እንዲላክ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።
አነስተኛ ጉዳዮችን በተመለከተ በተለይ ባለቀለም ሰዎች ለሚያንቀሳቅሷቸው ሥራዎች በተለየ ትኩረት እንደሚሰጥ የባይደን ዕቅድ ያሳያል። ዕቅዱን የሥልጣን ሽግግሩ ቡድን ግዙፍ እንደሆነ ጠቁሞ የማይቻል ግን አየደል ብሎታል። ይህንኑ የሚመስል ዕቅድ በቅርቡ የቀረበላቸው ሪፖብሊካን እንደራሴዎች እጅግ የበዛ ነው ሲሉ ውድቅ አድርገውት ነበር።