በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኮቪድ-19 በዓለም


ፎቶ ፋይል
ፎቶ ፋይል

በዓለም ዙሪያ እስከትናንት ማክሰኞ በነበረው የሰባት ቀን ጊዜ ውስጥ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን አዲስ የኮሮናቫይረስ ተያዦች የተገኙ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት አመለከተ። አርባ ሺህ ለህልፈት መዳረጋቸውን አክሏል።

አብዛኞቹ አዲሶች የኮሮናቫይረስ ተያዦች የተገኙት አውሮፓ ውስጥ መሆኑን የገለጠው ድርጅቱ ከቀደመው ሳምንት በሰላሳ ሶስቱ ከመቶ የጨመረ መሆኑን ነው ያመላከተው።

ሰሜን አሜሪካና እና ላቲን አሜሪካ እንዲሁም መካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካም ውስጥ የቫይረሱ ተጋላጮች ቁጥር እያሻቀበ መሆኑን የዓለሙ የጤ ድርጅት አስታውቋል። ደቡብ ምስራቅ እስያ አካባቢ ግን ስርጭቱ እየቀነሰ መሆኑን ነው ያወሳው።

ባለፈው ሳምንት ውስጥ ከፍተኛው የቫይረሱ ተጋላጮች ቁጥር የተመዘገበባቸው ሃገሮች ህንድ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ፈረንሳይ፣ ብራዚል እና ብሪታንያ መሆናቸውን የዓለሙ ድርጅት አክሎ አውስቷል።

የቫይረሱ ስርጭት የኒው ዮርኩን የተባበሩት መንግሥታቱን ድርጅት የሥራ እንቅስቃሴ ሳይቀር እያስተጓጎለ ነው። ትናንት የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዚዳንት ቮልካን ቦዚከር በካል የሚካሄዱ ስብሰባዎችን ሰርዘዋል። ይህ የሆነው በመንግሥታቱ ድርጅት የኒዠር ሚሽን ሰራተኞች የሆኑ አምስት ሰዎች ላይ ኮሮናቫይረስ መገኘቱን ተከትሎ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩናይትድ ስቴትስ ዙሪያ ባለፉት ሰባት ቀናት ብቻ አምስት መቶ ሁለት ሽህ ስምንት መቶ ሃያ ስምንት አዲስ የኮሮናቫይረስ ተያዦች ተመዝግቧል።

ቫይረሱ አብዝቶ እየተዛመተ ካለባቸው አካባቢዎች አንዷ የሆነችው የኢሊኖይ ክፍለ ግዛት አስተዳዳሪ በተለይ የሀገሪቱ ሦስተኛዋ ትልቅ ከተማ በሆነችው በቺካጎ አዲስ ዙር የቁጥጥርና ገደብ ርምጃዎች ማውጣታቸው ተሰምቷል።

በዚህም መሰረት ከፊታችን ዓርብ ጀምሮ ምግብ ቤቶችና ቡና ቤቶች ደጅ ብቻ እንጂ የቤት ውስጥ አገልግሎት እንዳይሰጡ ተከልክሏል።

የኮሎራዶዋ ዴንቨር ከተማም ዕሁድ ዕለት ሦስት መቶ ሃያ ሰባት አዲስ የቫይረሱ ተያዥች መመዝገባቸውን ተከትሎ ቀደም ሲል ሃምሳ ከመቶውን ደንበኞቻቸውን እንዲያስተናግዱ ተፈቅዶላቸው የነበሩት የምግብና መጠጥ ቤቶች ወደ ሃያ አምስት ከመቶ እንዲቀንሱ የከተማዋ ከንቲባ አዘዋል።

XS
SM
MD
LG