በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በሦስት ወንጀሎች ተከሰሰ


ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በሦስት ወንጀሎች ተከሰሰ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:49 0:00

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በሦስት ወንጀሎች ተከሰሰ

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በፍትሕ መጽሔት ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ ላይ ያቀረበው ክስ ሦስት የወንጀል ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ነው።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ የመሰረተውና ዛሬ ፍርድ ቤት ውስጥ በንባብ የተሰማው የክስ ዝርዝር፤ “ወታደራዊ ሚስጥሮችን ላልተፈቀደለት ሰው ወይም ለሕዝብ በመግለፅ”፣ ”የሐሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ በማሰራጨት” እና “መገፋፋት እና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር በመፈፀም” የሚሉ ሦስት የወንጀል ክሶችን ይዟል።

ዛሬ ሰኔ 22/2014 ዓ.ም በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ የሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ከተሰማው የወንጀሉ ዝርዝር ጉዳይ የመጀመሪያው ክስ “ወታደራዊ ሚስጥሮችን ላልተፈቀደለት ሰው ወይም ለሕዝብ በመግለፅ” የሚል ሲሆን ተመስገን በሚመራው ልሕቀት ሚዲያ ስር በሚታተመው ፍትሕ መጽሔት ላይ የወጡ ጽሑፎች በአስረጂነት ቀርበዋል።

በዚህ ክስ ማጠቃለያ ላይም፤ “መጽሔቱ ላይ በቀረቡት ጹሑፎች፤ በሀገሪቱ ክፍተኛ የፖለቲካና የጦር አመራሮች መካከል የተደረገ ሚስጥራዊ ውይይት እና የሃገሪቱን የጦር ኃይል እና መሳሪያ አቅም ለሕዝብ እና ላልተገቡ አካላት እንዲገለፅ አድርጓል” የሚል መደምደሚያ ሰፍሮበታል።

”የሐሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ በማሰራጨት” በሚለው ሁለተኛው ክስ ላይ የተለያዩ የመፅሔቱ እትሞች ተጠቅሰው መከላከያን በተመለከተ የተጻፉ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን ዘገባዎቹ እውነት መሆናቸው ሳይረጋገጥና ከመከላከያ ማጣራት ሳይደረግባቸው የወጡ በመሆናቸው በወንጀል ለመከሰስ ምክኒያት መሆኑ በክሱ ላይ ተዘርዝሯል።

“መገፋፋት እና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር በመፈፀም” በሚለው ሦስተኛ ክስ ላይም ትክክለኛ ያልህነ ጥላቻ የተሞላበት መረጃን በማሰራጨት ሕዝብ ያለውን አቋም የሚያፈርስ መረጃን አሰራጭቷል በሚል ክስ ቀርቦበታል።

በፍትሕ መጽሔት ላይ የታተሙትና ለክስ መነሻ ምኒያት ናቸው ከተባሉት ጹሑፎች መካከል

የካቲት 2014 ታትሞ የወጣው የቀድሞው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ የብርጋዴየር ጄነራል ተፈራ ማሞ ቃለ ምልልስ ጨምሮ፣ “ ሪፎርም ወይስ ፈረቃ”፣ “ወታደራዊ አመፅ ያሰጋል”፣ “ወታደራዊ ጉዳዮች”፣ “መከላከያ ተቋማዊ ወይስ ኔትወርክ”፣ “የጄኔራሉ ሚስጥሮች” እና “የጄኔራሉ መታፈንና አንደምታው” የሚሉ ጽሑፎች ይገኙበታል።

ክሱ በንባብ ከተሰማ በኋላ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በጽሑፎቹ ሐሳብን ከመግለጽና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማስቻ ጥረት ከማድረግ ባለፈ ወንጀል አለመፈጸሙን በመግለጽ የቀረቡበትን ክሶች አጣጥሏል፡፡

የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ በበኩላቸው ለችሎቱ የዋስትና ጥያቄ አቅርበው ክርክር የተደረገ ሲሆን ለአርብ ለውሳኔ ተቀጥሯል።

ከግንቦት 18/2014 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ “ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት ወንጀል” ተጠርጥረው ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩ የሚዲያ ባለሙያዎች መካከል ክስ የተመሰረተበት ብቸኛው ጋዜጠኛ ነው። ቀሪዎቹ በዋስትና የተፈቱ ሲሆን ፣ ከተፈቱት መካከል ያየሰው ሽመልስ በትናንትናው ዕለት በድጋሚ መያዙ ይታወሳል፡፡

XS
SM
MD
LG