በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢሰመኮ በሽብር ተከሳሾች የመብት ጥሰት አቤቱታ የመጨረሻ ምርመራውን እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት አዘዘ


ኢሰመኮ በሽብር ተከሳሾች የመብት ጥሰት አቤቱታ የመጨረሻ ምርመራውን እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት አዘዘ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:20 0:00

ኢሰመኮ በሽብር ተከሳሾች የመብት ጥሰት አቤቱታ የመጨረሻ ምርመራውን እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት አዘዘ

በእነአቶ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ የተካተቱ የሽብር ተከሳሾች ባቀረቡት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ላይ ለሚያደርገው ምርመራ፣ ኢሰመኮ ተጨማሪ ጊዜ ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡

ተከሳሾቹ፣ በቤተሰብ የምግብ አቅርቦት እና ጥየቃ ላይ “በማረሚያ ቤት ተጥሎብናል” ያሉት ገደብ፣ ከፍርድ ቤቱ ዳግመኛ ትዕዛዝ በኋላ መነሣቱን ለችሎቱ ገልጸዋል። ኾኖም፣ ገደቡ ሊቀጥል ይችላል፤ ብለው እንደሚሰጉ አመልክተው፣ ተጠያቂነት እንዲኖር አመልክተዋል፡፡

በእነአቶ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ የሽብር ክስ ከተመሠረተባቸው 52 ተከሳሾች መካከል፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ 16ቱ፣ ዛሬ ኀሙስ፣ ግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ጉዳያቸው እየታየ ባለበት፣ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ችሎት ቀርበዋል፡፡

የዛሬው ችሎት ከተቀጠረባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ ተከሳሾቹ፥ በአዋሽ አርባ እና በዐዲስ አበባ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ “ተፈጽመውብናል” ባሏቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አጣርቶ እንዲያቀርብ በፍርድ ቤት የታዘዘውን የምርመራ ውጤት ለመጠባበቅ ነበር፡፡

በችሎቱ የተገኙት፣ የኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዲሬክተር ሰላማዊት ግርማይን ጨምሮ ሦስት የኢሰመኮ ባልደረቦች፣ ምርመራው መጀመሩን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ምርመራ የሚካሔድባቸውን ቦታዎች ለመጎብኘትና ለተያያዥ የምርመራ ሒደቶች፣ ከሚመለከታቸው አካላት ፈቃድ ማግኘትን ጨምሮ ጊዜ የሚጠይቁ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ለኮሚሽኑ የአንድ ወር ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አቤቱታው በዝርዝር መቅረቡን የገለጹት ከተከሳሽ ጠበቆች አንዱ አቶ ሰሎሞን ገዛኸኝ፣ የኮሚሽኑን ባልደረቦች ማብራሪያ ያደመጠው ችሎቱ ተጨማሪ ጊዜ መፍቀዱን ጠበቃው ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ የምርመራ ሪፖርቱን እንዲያቀርበ በፍርድ ቤቱ የታዘዘው፣ ተከሳሾቹ በእስር ላይ እያሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንደተፈጸመባቸው በማመልከታቸውና ፖሊስ በማስተባበሉ ምክንያት ነው፡፡

በተመሳሳይ፣ ተከሳሾቹ፥ “የቤተሰብ ጥየቃ እና የምግብ አቅርቦትን ጨምሮ በማረሚያ ቤት እየተፈጸመብን ነው፤” ያሉትን የመብቶች ጥሰት አቤቱታ ተከትሎ፣ ችሎቱ የሰጠው ትእዛዝ አፈጻጸም ምን እንደሚመስል የተከሳሾቹን ቃል አድምጧል፡፡

ችሎቱ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ከመደበኛው የጊዜ ቀጠሮ በተለየ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎችን ምላሽ ማዳመጡን፣ ተከሳሾቹ በዛሬው የችሎት ውሎ አስታውሰዋል። በዕለቱ፣ በድጋሚ የመብቶች ጥሰት እንዳይፈጸም ፍርድ ቤቱ ካዘዘ በኋላ፣ አድሏዊ በኾነ መንገድ፣ በቤተሰብ ጥየቃ እና የምግብ አቅርቦት ላይ ተጥሎ ነበረ፤ ያሉት ገደብ መነሣቱን አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ተከሰሾቹን ወክለው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ኾኖም፣ ችግሩ ሊቀጥል ይችላል፤ የሚል ስጋት እንዳላቸውም ከጠበቆቻቸው መካከል የኾኑት አቶ ሰሎሞን አመልክተዋል፡፡ በዛሬው ችሎት ላይ፣ የተከሳሽ ጠበቆች የክስ መቃወሚያ ያቀረቡ ሲኾን፣ የዋስትና ክርክርም ተደርጓል።

የተከሳሽ ጠበቆች፣ በደንበኞቻቸው ላይ የቀረበው ክስ ዋስትና እንደማያስከለክል ያስረዱልናል ያሏቸውን የሕግ ድንጋጌዎች ጠቅሰው ሲከራከሩ፣ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ፣ የሽብር ክሱ ከ15 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል መኾኑን፣ እንዲሁም ተከሰሾቹ በዋስትና ከተለቀቁ “ወደ ጫካ በመሔድ አብረዋቸው የተከሰሱ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን ሊቀላቀሉና ሊያመልጡ ይችላሉ፤” በሚል ተከራክሯል።

ችሎቱ፣ በክስ መቃወሚያውና በዋስትናው ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት፣ ለፊታችን ሰኔ 12 ቀን ቀጥሯል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሦስት መዝገብ ተከፍለው፣ ትላንት ለመጀመሪያ ጊዜ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍረድ ቤት ልደታ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረቡት 112 የሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎች፣ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡

የዛሬው ችሎት የተቀጠረው፣ በሁለቱ መዝገቦች ዐቃቤ ሕግ፣ ክስ ለመመሥረት በጠየቀው የተጨማሪ የ15 ቀን ጊዜ እና ፖሊስ፣ በአንድ መዝገብ ሥር ባሉ 88 ተጠርጣሪዎች ላይ ለጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ፣ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡

ችሎቱም፣ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ለዐቃቤ ሕግ የተጠየቀውን የክስ መመሥረቻ ጊዜ በመፍቀድ፣ ለሰኔ 12 ቀን ሲቀጥር፤ በ88ቱ ተጠርጣሪዎች ፖሊስ ለጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ላይ ደግሞ ብይን ለመስጠት ለነገ መቅጠሩን አቶ ሰሎሞን ገዛኸኝ ተናግረዋል፡፡

ኹሉም ተጠርጣሪዎች፣ ትላንት በተጠናቀቀው የአስቸኳይ ዐዋጅ ዐውድ ውስጥ፣ በቁጥጥር ሥር ውለው በአዋሽ አርባ እና በዐዲስ አበባ በሚገኙ ማቆያዎች የነበሩ ናቸው፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG