በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ100 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲለቀቅ ተወሰነ


ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለለኝ
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለለኝ

በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሦስት የወንጀል ክሶች የቀረቡበት የ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ ዛሬ ሰኔ 27/2014 ዓ.ም የ100 ሺህ ብር ዋስትና አሲዞ ከእስር እንዲፈታ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ዋስትናውን የፈቀደው በአብላጫ ድምፅ ነው።

በተመስገን የዋስትና ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለዛሬ የቀጠረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት፣ የዋስትና ብይኑን በዳኞች የአብላጫ ድምጽ መስጠቱን ጠበቃው አቶ ሄኖክ አክሊሉ ገልጸዋል፡፡

ሁለት ዳኞች ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከእስር ተለቆ ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እንዲከታተል ሲወስኑ አንድ ዳኛ በሐሳብ ተለይተዋል፡፡

ሁለቱ ዳኞች የ100 ሺህ ብር ዋስትናውን የፈቀዱት ከዚህ በፊት የተደረጉ ክርክሮችን በመዳደሰስ መሆኑን አቶ ሄኖክ ገልፀዋል፡፡ ዳኞቹ በጋዜጠኛ ተመስገን ከቀረቡበት ክሶች መሃከል “ሁለቱ ክሶች ቀላል መሆናቸውን” በመግለጽ፣ እንዲሁም “ቢለቀቅ ሌላ ወንጀል ሊሠራ ይችላል” በሚል የቀረበውን መቃወሚያ በተመለከተ ደግሞ ሐሳብን በነጻነት መግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብት በመሆኑ “ከወዲሁ ክልከላ ሊደረግ አይችልም” በማለት የዋስትና ብይኑን መስጠታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ቋሚ አድራሻ ያለውና የዋስትና ግዴታውን አክብሮ ሊቀርብ የሚችል በመሆኑ፣ ቢለቀቅ ፍርድ ቤት ላይቀርብ ይችላል በሚል በዐቃቤ ሕግ የቀረበውን መቃወሚያም ሁለቱ ዳኞች ባለመቀበል ከውሳኔው ላይ መድረሳቸው ታውቋል፡፡

ሆኖም ክርክሩ በሚካሔድበት ጊዜ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ከሀገር እንዳይወጣ ለኢሚግሬሽን ትዕዛዝ እንደተሰጠ ፍርድ ቤቱ አሳውቋል፡፡

የተባለውን የ100 ሺሕ ብር ዋስትና አስይዘው መፈቻ ለማጻፍ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ከተመስገን ቤተሰቦች ባገኘነው መረጃ ለመረዳት ችለናል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የቀረቡበት ሦስት የወንጀል ክሶች “ወታደራዊ ሚስጥሮችን ላልተፈቀደለት ሰው ወይም ለሕዝብ መግለፅ”፣ ”የሐሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ ማሰራጨት” እና “መገፋፋት እና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር መፈፀም” የሚሉ ናቸው፡፡

ዛሬ የተሰጠው የዋስትና መብት ተፈጻሚ ከሆነ፣ ከግንቦት 18/2014 ዓ.ምጀምሮ በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ተመስገን የ100 ሺህ ብር ዋስ በማስያዝ ጉዳዩን በውጭ ሆኖ የሚከታተል ይሆናል፡

XS
SM
MD
LG