በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመዋጋት $8.3 ቢሊዮን ዶላር ተመደበ


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመዋጋት የሚውል ስምንት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር አስቸኳይ ወጪ የመደበውን ህግ ዛሬ በዋይት ሃውስ ፈርመዋል።

ኮሮናቫይረስ ከዋሽንግተን አቅራቢያ ሚሪላንድ ክፍለ ግዛት ውስጥ ወደሚገኝ አውራጃ ተዛምቷል።

የተመደበው ገንዘብ በቫይረሱ ለተጋለጡ ህክምና እና የመከላከያ ክትባት ፍለጋ ለክፍለ ግዛቶች እና የአካባቢ አስተዳደሮች ዕርዳታ የሚውል መሆኑ ተጠቁሟል።

በጀቱ የተፈቀደበትን ህግ የዩናይትድ ስቴትስ የመወሰኛው እና የተወካዮች ምክር ቤቶች ትናንት በሙሉ ድምጽ በሚባል ደረጃ አጽድቀውታል።

ከዋይት ሃውስ ጥቂት ደቂቃዎች ርቀት ላይ ምትገኘው የሚሪላንድ ሞንትጎመሪ ካውንቲ ውስጥ ትናንት የመጀመሪያ በቫይረሱ መጋለጣቸው የተረጋገጠ ሰዎች መገኘታቸው ተገልጿል። የክፍለ ግዛትዋ ሀገረ ገዢ ሌሪ ሆጋን ሦስት የቫይረሱ ተያዦች መገኘታቸውን ተከትሎ አስቸኳይ ጊዜ አውጀዋል።

በተያያዘ ዜና የዩናይትድ ስቴትስ የጤና እና የሰብዓዊ አገልግሎት ሚኒስትር አሌክስ አላዛር ትናንት በሰጡት መግለጫ አንድ ሚሊዮን የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ የያዙ ጥቅሎች በሳምንቱ መጨረሻ በየላቦራቶሪው ይደርሳሉ ብለዋል።

እስካሁን አምስት የዩናይትድ ስቴትስ ክፍለ ግዛቶች ካሊፎርኒያ ፍሎሪዳ ዋሺንግተን ሃዋይ እና አሁን ደግሞ ሜሪላንድ አስቸኳይ ጊዜ አውጀዋል።

ሜሪላንድ ዕርምጃውን የወሰደችው ሦስት የሞንትጎመሪ ወረዳ ነዋሪዎች በሰባዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ባልና ሚስት እና ሃምሳዎቹ ዓመታት ውስጥ ያሉ ሴት ኮሮናቫይረስ እንደተያዙ ከተረጋገጠ በኋላ ነው። ሦስቱም ሰዎች ቫይረሱ ያገኛቸው ውጭ ሃገር የመርከብ ሽርሽር ላይ ሳሉ እንደሆነ ተገልጿል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG