በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የካርቦን ልቀት መጠን ጨምሯል ተባለ⁣


በግብጿ መዝናኛ ከተማ ሻርም ኤል ሼክ እየተካሄደ ባለው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ
በግብጿ መዝናኛ ከተማ ሻርም ኤል ሼክ እየተካሄደ ባለው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ

ከቅሪተ አካል ነዳጆች ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን እአአ በዚህ ዓመት በአንድ ከመቶ መጨመሩን አንድ አዲስ ጥናት አመለከተ።⁣

በግብጿ መዝናኛ ከተማ ሻርም ኤል ሼክ እየተካሄደ ባለው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ የቀረበው አዲስ ጥናት መሪ የሆኑት የብሪታንያው ኤግዘተር ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ፒየር ፍሪድሊንግስታይን ሲናገሩ የካርቦን ልቀቱ መጠን እየጨመረ እንጂ የመቀነስ ምልክት እያሳየ አይደለም ብለዋል። ⁣

ለቀጣዮቹ ዘጠኝ ዓመታት በየዓመቱ ተመሳሳይ መጠን ያለው ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደከባቢ መለቀቁን ይቀጥላል ያሉት ሳይንቲስት እአአ 2031 አካባቢ ላይ አንድ ነጥብ አምስት ከመቶ ልቀት ደረጃ ላይ መድረሳችን አይቀርም ነው ያሉት።⁣

ሳይንቲስቶቹ በገመገሙት ዓመት ከወትሮው የተለየ ነገር ማስተዋልቸውንም በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል። ⁣

ቻይና ለዓመታት ካሳየችው እካሄድ በተለየ መልኩ ያለፈው ዓመት የካርቦን ልቀቷ መጠን መቀነሱን የጠቆመው ጥናቱ የዚህ ምክንያቱ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ እንቅስቃሴዎች መዘጋታቸው ሊሆን እንደሚችል አመልክቷል።⁣

የአውሮፓም አጠቃላይ የካርቦን ብክለት ቀንሶ መታየቱን የጠቀሰው አዲሱ ሪፖርት ሆኖም ከዩክሬን ጦርነት ወዲህ ከከሰል የሚመነጨው ልቀት እንደጨመረ አመልክቷል። ⁣

የዩናይትድ ስቴትስ የካርቦን ልቀት መጠን ደግሞ በ1 ነጥብ 5 ከመቶ ማደጉን የገለጸው ሪፖርቱ ዓለም አቀፉ የበካይ ጋዝ ልቀት እያሻቀበ ይሁን እንጂ ከአስር ወይም ከአስራ አምስት ዓመት በፊት በነበረው ደረጃ እንዳልሆነ ሳይገልጽ አላለፈም።⁣

ሪፖርቱ ባጠቃላይ የሚያስደምም ዜና የያዘ መሆኑን የሚናገሩ ሳይንቲስቶች የመሬት ሙቀት ከአንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴልሲየስ እንዳያልፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስምምነት ከተደረገበት ገደብ ሊያልፍ እየተቃረበ መሆኑን የሚጠቁም መሆኑን ያነሳሉ።⁣

XS
SM
MD
LG