ፕሬዝደንት ባይደን ለ100 ሀገራት ለመለገስ ቃል የገቡት ተጨማሪ 500 ሚሊዮን የፋይዘር ክትባት በመጪው ነሐሴ ወር መሰራጨት እንደሚጀምር ተገለጸ። ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪካ የምትለግሰውን የኮቪድ 19 ክትባት በተመለከተ በተካሔደ የበይነ መረብ ውይይት ላይ፣ ሀገሪቱ 25 ሚሊዮን ክትባት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለአፍሪካ ሀገራት በማድረስ ላይ መሆኗ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ፕሬዝደንት ባይደን ለ100 ሀገራት ለመለገስ ቃል የገቡት 500 ሚሊዮን የፋይዘር ክትባትም ከቀጣዩ ወር ጀምሮ እንደሚሰራጭ እና ከዚህም አፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ክትባት እንደምታገኝ የዩኤስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ኮቪድ -19 ምላሽ እና የጤና ደህንነት አስተባባሪ ጌይል ስሚዝ ተናግረዋል፡፡
የክትባቱን ምርት ለማሳደግ፣ በዩኤስ የሚገኙ የመድኃኒት አምራቾች ፣ የኮቪድ 19 ክትባትን ጨምሮ በአፍሪካ የሕክምና ግብዓቶችን እንዲያመርቱ ለማስቻል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በዩኤስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አኩና ኩክ በበኩላቸው፣ ለአፍሪካ እና ለመላው ዓለም በድጋፍ መልክ የሚሰጠው ክትባት ደህንነቱ የተጠበቀ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
አፍሪካ የተለያዩ ችግሮችን በመጋፈጥ ላይ ያለች አህጉር ብትሆንም፣ የኮቪድ ወረርሽኝን መቆጣጠር ካልተቻለ ለሌሎች ችግሮች ምላሽ መስጠት የማይቻል በመሆኑ፣ የባይደን አስተዳደር ለኮቪድ ምላሽ ቅድሚያ ሰጥቶ በመሥራት ላይ መሆኑንም ነው ረዳት ሚኒስትሯ አኩና ኩክ የገለጹት።
ለዝርዝሩ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።