በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኅዳሴ ጉዳይ የጥቁር እንደራሴዎች ጉባዔ መግለጫ አወጣ


የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት የጥቁር እንደራሴዎች ጉባዔ /ከንግሬሽናል ብላክ ኮከስ/
የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት የጥቁር እንደራሴዎች ጉባዔ /ከንግሬሽናል ብላክ ኮከስ/

የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት የጥቁር እንደራሴዎች ጉባዔ /ከንግሬሽናል ብላክ ኮከስ/ በታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ሰላማዊና ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበት ስምምነት ላይ እንዲደረስ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ በግንባታ ላይ /ፎቶ ፋይል/
ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ በግንባታ ላይ /ፎቶ ፋይል/


ምክር ቤቱ ይህንን አቋሙን ያሳወቀው ማክሰኞ፤ ሰኔ 16/2012 ዓ.ም. ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ሲሆን መልዕክቱን የጀመረው ድርድሮቹ ወደፊት መግፋት አለመቻላቸውንና በግድቡ ምክንያት በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን ላይ ጫና ሊያሳድር በሚችል ሁኔታ ውጥረት ማየሉን በማመልከት ነው።

በታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ሁሉም ባለድርሻዎች ባልተቋረጠ መተባበርና በሰላማዊ ድርድር እንዲገፉ የጥቁር እንደራሴዎቹ ጉባዔ እንደሚያበረታታ መግለጫው አስታውቋል።

ምክር ቤቱ አክሎም ድርድሮቹ በጋራ ተጠቃሚነት፣ በቅን ልቦናና በዓለምአቀፍ ሕግ መርሆች ላይ እንዲመሠረቱም አሳስቧል።

በብዙ ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ ነዋይ እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ መሠረት የተጣለው በ2003 ዓ.ም. እንደነበረ ያስታወሰው የጥቁር እንደራሴዎቹ ምክር ቤት መግለጫ ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትና ኢትዮጵያም ለጎረቤቶቿ ኃይል እንድታቀርብ የሚያስችላት በአፍሪካ ግዙፉ ግድብ ሆኖ ለአካባቢው አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው አስረድቷል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በግብፅ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን የውኃ ፍሰት፣ የኃይል አቅርቦትና የምግብ ዋስትና ላይ ቀጥተኛ ጫና እንደሚያሳርፍ መግለጫው አመልክቶ የአካባቢው ግብርና ወቅቱን የማይጠብቅ የዝናብ ሁኔታ በሚያስከትለው ድርቅ መጎዳቱንም አስታውሷል።

በማስከተልም በፍጥነት እያደገ ወደ መቶ ሚሊየን እየተጠጋ ላለው የግብፅ ሕዝብ ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የውኃ አቅርቦቱን እንደሚያሻሽልና ሃገሪቱ የበዛውን ወራጅ ውኃዋን ከምታገኝበት ከአባይ ወንዝ ላይም ግፊቱን እንደሚያቃልል ጠቁሟል።

ኢትዮጵያ አሁን ከሕዝቧ ወደ ሃያ ከመቶ የሚሆነውን በቀጥታ የሚጎዳ ድርቅና በቅርብ ወራትም ከሦስት መቶ ሃያ ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር ባላይ የሚሆን እርሻ ላይ የዋለ ሰብል ያጠፋ የአንበጣ መንጋ መጋፈጧን የእንደራሴዎቹ መግለጫ ይናገራል።

ሱዳንን በተመለከተ ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የሃገሪቱን የውኃ አጠቃቀም ለማስተካከል፣ ደለል ለመቀነስና የግብርና ፕሮጀክቶችን ለማስፋት፣ ኃይል የማመንጨት አቅሟን ለመጨመርና በምግብ ላይም ቁጥጥር እንዲኖራት በማስቻል እንደሚያግዝ አመልክቷል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በጉዳዩ ውስጥ ላሉ ሃገሮች ሁሉ ጥቅም እንደሚኖረው፣ የምግብ ዋስትና ችግርን ለመዋጋት፣ የኤሌክትሪክና የኃይል አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል፣ ቁጥሩ ከአሁኑ የበዛ ሕዝብ የተሻለ መጠን ያለው የውኃ ፍሰት እንዲያገኝ፣ የአካባቢውን ምጣኔ ኃብቶችም ለማረጋጋትና ዕድገት እንዲኖር ለማድረግም እንደሚያግዝ መግለጫው ያስረዳል።

የግድቡ ፕሮጀክት ተግባራዊ እንዲሆን ሰላማዊ ድርድሮች እንዲካሄዱ የተወካዮች ምክር ቤቱ የጥቁር እንደራሴዎች ጉባዔ ድጋፉን እንደሚሰጥ መግለጫቸው አስታውቆ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ስምምነት ላይ በሰላማዊ መንገድ እንዲደረስ ለማድረግ የአፍሪካ ኅብረትንና ሁሉንም ባለድርሻዎች ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

በኅዳሴ ጉዳይ የጥቁር እንደራሴዎች ጉባዔ መግለጫ አወጣ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:35 0:00


XS
SM
MD
LG