በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዴሞክራቲክ ኮንጎ አማጺያኑ እያየሉ ባሉበት ሰዓት ከሩዋንዳ ጋር ያላትን ግንኙነት አቋርጣለች


ከዴሞክራቲክ ኮንጎፕ ጎማ ከተማ ዜጎች ለቀው ሲወጡ፤ ጥር 18/2016 ዓ.ም
ከዴሞክራቲክ ኮንጎፕ ጎማ ከተማ ዜጎች ለቀው ሲወጡ፤ ጥር 18/2016 ዓ.ም

በሩዋንዳ በሚደገፉት አማፂያን እና በዴሞክራቲክ ኮንጎ መንግስት ኃይሎች መካከል፤ ቁልፍ በሆነችው ጎማ ከተማ ምሥራቃዊ ክፍል ጦርነት የተቀሰቀሰ ሲሆን፣ በትንሹ 13 የሰላም አስከባሪ ሃይሎች እና የውጭ ሃገር ወታደሮች ህይወታቸው ሲያልፍ፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ተፈናቅለዋል። ዴሞክራቲክ ሪፐሊክ ኮንጎም ከሩዋንዳ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጣለች።

የኤም 23 አማፂ ቡድን ከሩዋንዳ ጋር በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች መኖሪያ እና የሰብዓዊና የጸጥታ ማዕከል ወደ ሆነችው ወደ ጎማ ግዛት በመገስገስ ብዙ ስፍራዎችን ተቆጣጥሯል።

ኮንጎ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለሞያዎች፤ ሩዋንዳ ከአስር ዓመት በፊት ከኮንጎ ጦር ሰራዊት ተገንጥለው በወጡ ቱትሲዎች የሚመራውን ኤም23ን ትደግፋለች ሲሉ ወቅሰዋል። ይህም በዋናነት በማዕድን በበለፀገው ክልል ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት በመቶዎች የሚቆጠሩ የታጠቁ ቡድኖች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ሁኔታው ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ግጭት በመፍጠር ከዓለም ትልቁ ሰብዓዊ ቀውስን አስከትሏል።

የዴሞክራቲክ ኮንጐ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትላንት ቅዳሜ ማምሻውን ሀገራቸው ከሩዋንዳ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጧን በመግለጽ በሩዋንዳ የሚገኙ ሁሉም የኮንጎ ዲፕሎማቲክ ሰራተኞች ከሀገሪቱ “በአፋጣኝ” እንዲወጡ መወሰኑን ተናግረዋል። ሩዋንዳ በጉዳዩ ላይ ወዲያውኑ አስተያየት አልሰጠችም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG