ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ውስጥ እስረኞች ከወህኒ ቤት ለማምለጥ ሲሞክሩ 129 ሰዎች መገደላቸው ተገለጠ።
የመንግሥቱ ቃል አቀባይ በኤክስ ገጻቸው ላይ እንዳስታወቁት የጸጥታ ኅይሎች ትላንት ሰኞ ማለዳ በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ከሚገኘው ከትልቁ ወህኒ ቤት እስረኞች ሰብረው ሊያመልጡ ሲሉ ከባድ ተኩስ ተነስቷል። የጸጥታ ኃይሎች የወህኒ ቤቱን አካባቢ አጥረውታል።
ከወህኒ ቤቱ የወጡ ምስሎች 24 ሊያመልጡ የሞከሩ እስረኞች እጅግ ከተጨናነቀው የማካላ ማዕከላዊ እስር ቤት ትላንት ሰኞ ሊያመልጡ ሲሞክሩ በጥይት ተመትተው መገደላቸውን አመልክቷል፡፡
ወህኒ ቤቱ ውስጥ የተቀረጹ እንደሆኑ የተገለጹ ነገር ግን ያልተረጋገጡ የቪዲዮ ምስሎች መሬት ላይ የወደቁ በርካታ አስከሬኖችን አሳይተዋል፡፡
በኮንጎ ትልቁ የሆነው እና 1500 ሰዎችን ብቻ መያዝ የሚችለው የማካላ ወህኒ ቤት አብዛኞቹ ጉዳያቸው በክስ ሂደት ውስጥ ያለ 12 ሺህ እስረኞች እንደሚገኙበት አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል፡፡ ከእስር ቤቱ በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም በጎርጎርሳዊያኑ 2017 በአንድ የሃይማኖት ቡድን በተፈጸመ ጥቃት ብዙዎች አምልጠዋል፡፡
ለማምለጥ የተደረገው ሙከራ ከእስር ቤቱ ውስጥ በአንድ ክንፍ ውስጥ ባሉ እስረኞች የተቀነባበረ ሴራ መሆኑን ምክትል የፍትህ ሚኒስትር ምቤምባ ካቡያ ለአካባቢው ቶፕ ኮንጎ ኤፍ ኤም ራዲዮ ተናግረዋል።
ማካላ - በኮንጎ ከሚገኙ እስር ቤቶች መካከል - በጣም የተጨናነቀ ከመሆኑ የተነሳ ብዙውን ጊዜ እስረኞች በረሃብ ይሞታሉ ሲሉ የማህበራዊ ኑሮ ጉዳይ ተሟጋቾች ይናገራሉ። በዚህ የአውሮፓዊያን ዓመት መግቢያ ላይም የእስር ቤቶችን መጨናነቅ ለማስወገድ ተብሎ በርካታ እስረኞች ተለቅቀዋል።
የፍትህ ሚኒስትሩ ኮንስታንት ሙታምባ ጥቃቱን “በዕቅድ የተቀነባበረ የጥፋት ተግባር” ሲሉ ገልጸው “እነዚህን የጥፋት ድርጊቶች ያነሳሱ’ ከባድ ቅጣት ይጠብቃቸዋል" ሲሉም ዝተዋል፡፡
መድረክ / ፎረም