በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በለገደንቢ የወርቅ ማውጫ ብክለት ቸልታ ሂዩማን ራይትስ ዋች ኩባንያዎችን ወቀሰ


ሂዩማን ራይትስ ዋች
ሂዩማን ራይትስ ዋች

ሂዩማን ራይትስ ዋች ችላ በተባለው የለገደንቢ የወርቅ ማዕድን ማውጫ መርዛማ ፍሳሽ ብክለት የነዋሪዎች ጉዳት በመቀጠሉ ኩባንያዎችን ወቀሰ።

በኢትዮጵያ የኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን የሻኪሶ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የለገደንቢ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ሥፍራ፣ ለዓመታት በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የጤና ጉዳት እያደረሰ ቢቆይም፣ “ኩባንያዎቹ ምንም ዐይነት የማስተካከያ ርምጃ ሳይወስዱ ቀርተዋል፤” ሲል ሂዩማን ራይትስ ዋች ወነጀለ፡፡

የሰብአዊ መብቶች ድርጅቱ፣ ዛሬ በአወጣው ሪፖርቱ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ የተካሔደው ክትትል፣ በለገደንቢ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ስፍራ ያለው ብክለት በነዋሪዎቹ ላይ ከባድ የጤና ጉዳት እንዳስከተለ ቢያሳይም፣ የወርቅ ማዕድን በማውጣት ሥራ ላይ የተሠማራው ሚድሮክ ኢትዮጵያ ኩባንያ እና ወርቅ የሚቀበለው የስዊዘርላንዱ አርጎር ሄሬየስ፣ አንዳችም የማስተካከያ ርምጃ አለመውሰዳቸውን ወቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት፥ የብክለቱ ጉዳይ እስከሚስተካከል ድረስ፣ የኩባንያው የሥራ ፈቃድ እንደሚታገድ አስታውቆ እንደነበር ያወሳው የሰብአዊ መብቶች ድርጅቱ፣ ኾኖም፣ “ሚድሮክ የማስተካከያ ርምጃ ሳይወስድ ፈቃዱ ተሰጥቶት ሥራውን ቀጥሏል፤” ብሏል፡፡

የወርቅ ማዕድን መውጫ ሥፍራው ብክለት በሚያደርሰው የጤና ጉዳት ምክንያት፣ በአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ በመቀስቀሱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እ.አ.አ በ2018 ግንቦት ወር ላይ፣ የለገደንቢ የወርቅ ማዕድን አውጪ ኩባንያውን የሥራ ፈቃድ አግዶ እንደነበር ሂዩማን ራይትስ ዋች በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የተካሔደው ሳይንሳዊ ምርምራ፣ ነዋሪዎቹ ለመርዛማ ንጥረ ነገሮች መጋለጣቸውንና ኹኔታው በጤናማ እና ንጹሕ አካባቢ የመኖር መብታቸውን እንደሚጥስ በጥናቱ እንደተደረሰበት አመልክቷል፡፡

መንግሥት፣ መርዛማው ፍሳሽ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የሚያግድ ርምጃ ሳይወሰድ፣ ኩባንያው የወርቅ ማውጣት ሥራውን እንዲቀጥል እንደማይፈቅድ አስታውቆ ነበር፤”

“መንግሥት፣ መርዛማው ፍሳሽ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የሚያግድ ርምጃ ሳይወሰድ፣ ኩባንያው የወርቅ ማውጣት ሥራውን እንዲቀጥል እንደማይፈቅድ አስታውቆ ነበር፤” ያለው ሂዩማን ራይትስ ዋች፣ ኾኖም ኩባንያው፣ እ.አ.አ. በ2021 ዓ.ም. ብክለቱን የሚቀንስ የማስተካከያ ርምጃ ሳይወሰድ፣ ሥራውን እንዲቀጥል መፈቀዱን አመልክቷል፡፡

የወርቅ ማዕድን ማውጫው አካባቢ ነዋሪዎች በተለይም ሕፃናቱ እየታመሙ፣ ለአካል ጉዳተኝነትም እየተጋለጡ መኾኑን በመግለጽ፣ ለዓመታት ሮሮ ሲያሰሙ መቆየታቸውን የዘገበው ሮይተርስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ኩባንያው፣ ተገቢውን የብክለት መቀነሻ ርምጃ እስከሚወስድ፣ የማዕድን ማውጫውን መዝጋት እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ሚድሮክ እና የስዊሱ ኩባኒያ አርጎር ሄሬየስ፣ ለነዋሪዎቹ የጉዳት ካሳ እና ሕክምና መስጠት፣ የተበከሉትን አካባቢዎችም ማጽዳት እንደሚገባቸው አመልክቷል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዋች፣ በሪፖርቱ ዝግጅት፥ 26 የአካባቢውን ነዋሪዎች፣ የቀድሞ የሚድሮክ ሠራተኞች፣ እንዲሁም የቀድሞ የአካባቢ እና የክልል ባለሥልጣናትን፣ የጤና እና የአካባቢ ጥበቃ ኤክስፐርቶችን ማነጋገሩን አስታውቋል፡፡ ብክለቱን በሚመለከት የተደረጉ ጥናቶችንም መመልከቱን አክሏል፡፡ ስለ ጉዳዩ፣ ሚድሮክ ኩባንያን መረጃ እንዲሰጥ ጠይቆ ምላሽ አለማግኘቱን፣ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቱ ጠቁሟል፡፡

ከዓለም ዋና ዋና ወርቅ አንጣሪ ኩባንያዎች አንዱ የኾነው አርጎር፣ እ.አ.እ. ከ2013 እስከ 2018 ከለገ ደንቢ የሚወጣ ወርቅ ሲቀበል እንደነበር ይናገራል፡፡ በሚድሮክ የ2007 ዓ.ም. ዓመታዊ ሪፖርት ላይ፣ ብቸኛው የቢዝነስ ሸሪኩ አርጎር መኾኑን ያሳያል፡፡

አርጎር፣ ለሪፖርቱ በሰጠው ምላሽ፣ ሪፖርቱ እጅግ ያስደነገጠው መኾኑን አመልክቶ፣ “ከአምስት ዓመታት በፊት በአካባቢው ስላለው ችግር እንዳወቅን ወዲያውኑ ከሚድሮክ ጋራ ያለንን ግንኙነት አቋርጠናል፤” ሲል በደብዳቤ ማሳወቁን ሂዩማን ራይትስ ዋች ተናግሯል፡፡

በዓለም ዙሪያ እንዲህ ለመሰሉ ጉዳዮች ተገቢውን ጥብቅ ትኩረት እና ክትትል ከሚያደርጉ ኩባንያዎች አንዱ መኾኑ የተነገረው የስዊሱ ኩባኒያ፣ “አጋጣሚው፣ የውስጥ አሠራራችንን ለመገምገም ዕድል ይሰጠናል፤” ማለቱን የጠቀሰው ሂዩማን ራይትስ ዋች፣ ሚድሮክም በአርጎር ሃሪዮስ እገዛ፣ ግልጽ የአካባቢ ጥበቃ ርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል” ሲል አሳስቧል፡፡

XS
SM
MD
LG