“ቡናማው ጭልፊት” በሚባል ተቀጥያ የጀብዱ ስም የሚጠሩት ኮሎኔል ሮቢንሰን በኢትዮጵያና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር እጅግ የጎላ ሚና መጫወታቸው ይነገርላቸዋል።
ኮሎኔል ሮቢንሰን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተቀሰቀሰባቸው የመጀመሪያ ዓመታት የግርማዊነታቸውን አየር ኃይል ለመመሥረትና ለማጠናከር ከፍተኛና የተዋጣ እገዛ ያደረጉ ከመሆኑም በላይ ዛሬ ሥማቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በስኬትና በጥንካሬ ከሚጠራ ገናና አየር መንገዶች አንዱ ለሆነውና በአፍሪካ አቪየሽን ግዙፉና ግንባር ቀደሙ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መፈጠር መሠረት የጣሉ ባለሙያ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል።
ኮሎኔል ሮቢንሰን ኢትዮጵያ ውስጥ ሲያከናውኗቸው የነበሩ ውጤታማና ፋና ወጊ ተግባሮች አሜሪካም ውስጥ እየታወቁና ልዩ ትኩረት እያገኙ በመምጣታቸው በዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይሎች ውስጥ በሚያገለግሉ ጥቁር ወታደሮች ላይ የነበረው የተዛባ አመለካከት በጠንካራ ገፅታ እንዲለወጥና የሚገባውቸውን ክብር እንዲያገኙ የጎላ አስተዋፅዖ ማበርከቱን አዲስ አበባ የሚገኘው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ዛሬ ያወጣው የፕሬስ መግለጫ ያስታውሳል።
በዚህም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ የተባበሩት ኃይሎች በሰሜን አፍሪካና የጣልያን የጦር አውድማዎች ላይ ለተቀዳጇቸው አንፀባራቂ ድሎች ጉልሁን ገድል የፈፀሙ ጥቁር አሜሪካዊያን ጄት አብራሪዎች ብቻ የተሣተፉበት የተስኪጊ የአየር ተዋጊዎች ግዳጅ እንዲሠማራ “ቡናማው ጭልፊት” ምክንያት ሆነዋል።
ያኔ በኮሎኔል ሮቢንሰን የተቋጠረው ግንኙነት ዛሬ በአቪዬሽን መስክ ኢትዮጵያና ዩናይትድ ስቴትስ አጠናክረው ለቀጠሉት የንግድና የደኅንነት ትስስር፣ እንዲሁም የአየር ጣቢያዎች አስተማማኝነት የተቀናጁ ሥራዎች መሠረት የጣለ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የአሜሪካ ኩባንያዎችና የዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ ተቋማት ትብብሮቻቸውን ማፅናታቸውና ማጥበቃቸውን የኤምባሲው የፕሬስ መግለጫ ይጠቁማል።
በአሜሪካና በኢትዮጵያ አየር ኃይል መካከል እየተካሄደ ባለው ጠንካራ ግንኙነት ኢትዮጵያ የምትጫወታቸውን የአካባቢያዊ የሰላም ጥበቃና ሰብዓዊ ክንዋኔዎች ለመደገፍ ዩናይትድ ስቴትስ በቅርቡ ለኢትዮጵያ አየር ኃይል ሲ-130 ኸርክዩለስ የማመላለሻ አይሮፕላን መላኳ ስለ ኮሎኔል ጆን ሲ ሮቢንሰን ውርስና ትሩፋት እማኝነት እንደሚቆም ኤምባሲው አመልክቷል።
ጉለሌ መካነ-መቃብር በሚገኘው "የኢትዮጵያ አቪዬሽን አባት" ኮሎኔል ራቢንሰን መታሰቢያ ኃውልት ላይ የአበባ ጉንጉን ሲቀመጥ ሥነ-ሥርዓቱ የተመራው በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን የአዲስ አበባ ሜትሮፖሊታን ጠቅላይ ሃገረ-ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ደመረው ሱራፌልና በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሣደር ማይክል ራይነር ነበር።
በመታሰቢያው ሥነ-ሥርዓት ላይ በተጨማሪም ከዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይሎች የአውሮፓና የአፍረካ ዕዙ ብሪጋዲየር ጄነራል ዲተር ባሬይስ፣ ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ብሪጋዲየር ጄነራል አስፋው ማመጫ፤ እንዲሁም የኮሎኔል ሮቢንሰንን ምንጭ ግዛትና ሌሎችም የዩናይትድ ስቴትስ ጦር አካላት በመወከል የሚሲሲፒ ብሄራዊ ዘብ አባላት ተገኝተዋል።
ጆን ቻርልስ ሮቢንሰን፤ ኅዳር 17 / 1896 ዓ.ም. በፍሎሪዳዋ ካራቤል ተወለደ። ኮሎኔል ጆን ቻርልስ ሮቢንሰን፤ መጋቢት 17 / 1946 ዓ.ም. በሃምሣ ዓመት ዕድሜአቸው አዲስ አበባ ላይ አረፉ።
የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ