የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ የሚያደርገው በረራ “መስተጓጎሉን” ዛሬ አስታወቀ።
በረራው የተስተጓጎለው በናይሮቢው ጆሞ ኬንያታ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ “በመካሄድ ላይ ባለው የሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ” ሳቢያ መሆኑን አየር መንገዱ ዛሬ ረቡዕ በቀድሞ ትዊተር ባሁኑ ኤክስ ላይ ባሰፈረው መልዕከት ጠቅሷል።
"የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተፈጠረው መስተጓጎል እና ችግር ከልብ ይቅርታ ይጠይቃል" ሲልም በመልዕክቱ አስፍሯል።
የአየር ማረፊያ ሠራተኞች አድማ የተቀሰቀሰው ‘የኬንያ መንግስት አውሮፕላን ማረፊያው በአንድ የህንድ ኩባንያ እንዲተዳደር የታቀደውን የኪራይ ስምምነት አስመልክቶ ያደረጉትን ተቃውሞ ተከትሎ ነው’ ሲሉ የብዙኃን መገናኛ የሚዲያ አውታሮች ዘግበዋል።
የጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኬንያም ሆነ በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የትራንስፖርት መናኻሪያ ነው።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ያደረጉት የሥራ ማቆም አድማ የአውሮፕላን ማረፊያው ሥራዎች እንዲቆሙ ማድረጉን የኬንያ ዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡
የተቃውሞ ሰልፉ አውሮፕላኖች እንዳይነሱ ማድረጉን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገደኞችም በከጉዟቸው እንዲስተጓጎሉ ማድረጉን ዘገባዎች ጨምረው አመልክተዋል፡፡
መድረክ / ፎረም