የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ ዛሬ ማክሰኞ ወደቱርክ እንደሚጓዙ የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት ገለጹ። ማህሙድ ወደ አንካራ የሚያቀኑት የቱርክ ፕሬዝደንት ሬቺፕ ታዪብ ኤርዶዋን ጋብዘዋቸው መሆኑን ባለሥልጣናቱ አመልክተዋል።
የአሜሪካ ድምፅ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት ያነጋገራቸው ሁለት ከፍተኛ የሶማሊያ ባለሥልጣናት እንዳሉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድም ወደአንካራ እንደሚሄዱ ይጠበቃል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ሁለቱ ባለሥልጣናት ለቪኦኤ እንደገለጹት ሁለቱ መሪዎች ከፕሬዝደንት ኤርዶዋን ጋር በተናጠል ተገናኝተው ይነጋገራሉ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እና ፕሬዝደንት ማህሙድ ከቱርኩ መሪ ጋራ በተናጠል ከተወያዩ በኋላ ፊት ለፊት የሚገናኙበት ሁኔታ ሊኖር ይችል እንደሆነ የተጠየቁት ባለሥልጣናቱ ከማረጋገጥም ኾነ ከማስተባበል ተቆጥበዋል ።
ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ስለቱርክ ጉዞው ጉዳይ አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የባሕር በር መግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ቀጥሏል።
ባለፉት ሐምሌ እና ነሐሴ ወራት ቱርክ ውስጥ የተደረጉት ሁለት ንግግሮች አለመግባባቱን ለመፍታት ሳይችሉ የቀሩ ሲሆን በመስከረም ወር ሊቀጥል ታቅዶ የነበረው ሦስተኛው ንግግር መዘግየቱ ይታወሳል።
በቅርቡም የኬኒያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ ከዩጋንዳ ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ጋር ሆነው ሁለቱን መሪዎች ለማነጋገር ዕቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም