በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለም የምግብ ዋጋ አሣሣቢ ሆኗል


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ሮድሃም ክሊንተን ሮም በተካሄደው የተመድ የምግብና የግብርና ድርጅት ስብሰባ ላይ ስለዓለም የምግብ ዋጋ ንረትና የመፍትሔ ሃሣቦች ዓርብ ሚያዝያ 28 ቀን 2003 ዓ.ም ንግግር ሲያደርጉ
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ሮድሃም ክሊንተን ሮም በተካሄደው የተመድ የምግብና የግብርና ድርጅት ስብሰባ ላይ ስለዓለም የምግብ ዋጋ ንረትና የመፍትሔ ሃሣቦች ዓርብ ሚያዝያ 28 ቀን 2003 ዓ.ም ንግግር ሲያደርጉ

የዓለምን የምግብ ዋጋ ንረት ለመቆጣጠርና የሕዝቦችንና የማኅበረሰቦችን ደህንነት ለማረጋገጥ ፈጣንና የተባበረ ጥረት እንደሚያስፈልግ ሂላሪ ክሊንተን አሳሰቡ፡፡

የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ በጣልያኗ ላ'አኪላ ከተማ ተሰብስበው የነበሩ የዓለም መሪዎች በግብርና ላይ የሚያፈስሱትን መዋዕለ ነዋይ ለማሣደግና ለማጠናከር፣ የዓለምንም የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ ቃል ገብተው እንደነበር ይታወሣል፡፡

ይሁን እንጂ ከመጋቢት በፊት በነበሩት ስምንት ተከታታይ ወራት የዓለም የምግብ ዋጋ በከፍተኛ መጠን እያሻቀበ መጥቶ መጋቢት ውስጥ መውረዱን የዓለም የምግብና የግብርና ድርጅት (ኤፍኤኦ) ባለፈው ሣምንት ውስጥ አስታውቋል፡፡

በኤፍኤኦው የዓለም የምግብ ዋጋ ማሣያ ሠንጠረዥ ንረቱ ሚያዝያ ውስጥ ረገብ ያለ ቢመስልም ባለፈው ዓመት በተከታታይ ጊዜ ከነበረበት መጠን ግን በ36 ከመቶ ያሻቀበ ነው፡፡ ከዋጋው ጣሪያ ከሢሦ በላይ ማለት ነው፡፡ ናረ ከተባለበት ከዚህ ዓመቱ የየካቲት ግለትም ቢሆን 'ምግብ ረከሰ፣ ወይም ቀነሠ' በተባለበት በሚያዝያ ቀንሶ ቀንሶ የታየው በሁለት ከመቶ ብቻ ነው፡፡

የዋጋው ሠንጠረዥ የመረጋጋት ምልክት እንዲያሣይ የረዱት የስኳርና የሩዝ ዋጋዎች መውረድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሌሎቹ የምግብ አቅርቦቶች ላይ ሁሉ በመላው የዓለም ገበያ ዋጋው ዛሬም እንደተሰቀለ መሆኑን የዓለሙ የምግብና የግብርና ድርጅት ሪፖርት ጠቁሟል፡፡

የኤፍኤኦው የንግድና ገበያ መምሪያ ኃላፊ ዴቪድ ሃላም ለዚህ የዋጋ ንረት እንደመንስዔና እንደሞተርም ያስቀመጡት የአሜሪካ ዶላር የምንዛሪ አቅም በተከታታይ መዳከም እና የነዳጁ ዋጋ ያለማቋረጥ ማሻቀብ ናቸው፡፡ ዋጋው እንዲያ አብዝቶ እየጎዳው ያለው ደግሞ የሰብሉን ገበያ ነው፡፡

"የምግብ ፍላጎቱ እየበረታ በመጣበት ጊዜ - አሉ ዴቪድ ሃላም - የዓለም የምግብ ዋጋ የመረጋጋቱና ወደመደበኛ ሥፍራው የመመለሱ ጉዳይ ዛሬ በአብዛኛው የሚመረኮዘው በያዝነው የአውሮፓዊያኑ 2011 ዓ.ም ምን ያህል ምግብ እናመርታለን? ምን ያህልስ የሰብል ጥሪት በዚህ መኸር እናከማቻለን? የሚሉ ጥያቄዎችን በመመለስ ላይ ነው፡፡"

ባለፈው ሣምንት ዓርብ ዋና ፅ/ቤታቸው ሮም ከሚገኙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ተቋማት መሪዎች ጋር የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን ተገናኝተው ነበር፡፡

ክሊንተን በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር የችግሩን አሣሣቢነትና ሥጋታቸውንም አጉልተው ያሣዩ ሲሆን በመላው ዓለም የሚታየው የዋጋ ንረትና የምግቡም እጥረት አለመረጋጋትን ለማብዘትና ለማስፋፋትም ሰበብ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡

ዝርዝሩን ከዘገባው ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG