በቻድ ሐይቅ አካባቢ ድርቅ፣ ጎርፍና የሐይቁ እየደረቀ መምጣት ግጭት፣ መፈናቀልና ስደት እንዲባባሱ እያደረጉ መሆናቸውን
ሬፍዩጂስ ኢንተርናሽናል የሚባል ድርጅት ዛሬ ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ።
የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ ሬፍዩጂስ ኢንተርናሽናል በዚሁ ሪፖርቱ ላይ በመጭው ሣምንት ኒዠር ዋና ከተማ ኒያሜ ላይ የቻድ ሐይቅ ሸለቆን ጉዳይ በተመለከተ የሚከፈተው ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ሥጋቱን አቢይ ትኩረቱ ሊያደርገው እንደሚገባ አሳስቧል።
የቀጣናው የአየር ንብረት እየተበላሸ መምጣት የተፈጥሮ ሀብት እንዲመናመን እያደረገው በመሆኑ ውጥረቱ እየከፋ መሆኑን ሪፖርቱ ጠቁሞ ብዙ ሰው ለመፈናቀልና ለስደት መዳረጉን አመልክቷል።
ሦስት ሚሊዮን ሰው ከመኖሪያው መፈናቀሉንና 11 ሚሊዮን ዕርዳታ ጠባቂ መሆኑን ሪፖርቱ ገልጿል።
ቻድ ሐይቅ በስድሣ ዓመታት ውስጥ ባልታየ ደረጃ 90 ከመቶው መድረቁን የተባበሩት መንግሥታት የተፈጥሮ አካባቢ ጉዳይ ቢሮ ማሳየቱን ሬፍዩጂ ኢንተርናሺናል በሪፖርቱ ላይ ጠቅሶ ዋናው ምክንያት የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑን አመልክቷል።