የመጀመሪያውን የኮሮናቫይረስ ተያዥ ማግኘቱን የሶማሊያ መንግሥት ዛሬ አስታወቀ። የጤና ሚኒስትሯ ፎዚያ አቢካር ሞቃዲሾ ውስጥ ባደረጉት ጋዜጣዊ
ጉባዔ ወረርሽኙ ካለባቸው ሃገሮች መካከል ከአንዱ የተመለሰ ሶማሊያዊ ቫይረሱ እንዳጠቃው በምርመራ ተረጋግጧል ብለዋል።
ኮሮናቫይረስ በብዛት ከተዛመተባቸው ሃገሮች የተመለሱ ዜጎቻችን ለጥንቃቄ አውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ እንዲቆዩ አድርገን ነበር። እናም ናሙና ለምርመራ ተወስዶ ዛሬ ጠዋት ባገኘነው ውጤት መሰረት እንድ ሰው ለቫይረሱ የተጋለጠ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል።
የሶማሊያ መንግሥት የግለሰቡን ማንነት አይግለፁ እንጂ ባለፈው ሳምንት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ከቻይና የመጡ ሶማሊያውያን ለይቶ ማቆያ ውስጥ ይዘናቸዋል ሲል አስታውቆ ነበር።
ሶማሊያ ለበርካታ ዓመታት በሁከትና በህግ አልባነት የታመሰች በመሆኗ ይህ ነው የሚባል የጤና ጥበቃ ሥርዓት ስለሌላት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተባት ከባድ መቅሰፍት ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ቫይረሱ እንዳይዛመት የሶማሊያ መንግሥት ለሁለት ሳምንታት ዓለምቀፍ በረራዎች ከሃገርዋ እንዳይወጡም እንዳይገቡም አግዳለች። ከነገ ወዲያ ረቡዕ የሚጀምረው የበረራ ዕገዳው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኬንያ፣ የዩጋንዳ፣ የቱርክ እና የካታር አየር መንገዶችን ጨምሮ ከእና ወደሶማሊያ የሚበሩ ዓለምቀፍ አየር መንገዶችን ይመለከታል። በየቀኑ ወደሶማሊያ ጫት ጭነው የሚጓዙ በርካታ የኬንያ አውሮፕላኖችንም ይከለክላል። ለሰብዓዊ ረድዔት በረራዎች የተለየ ፈቃድ እንሰጣለን ሲል የሶማሊያ መንግሥት አስታውቋል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ