በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፕሬዚዳንት ሺ “ሀገራትን ከቻይና መነጠል” ያሉትን የምዕራባውያን ጥረት ተቹ


የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ፣
የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ፣

የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ፣ “በቻይና ኢኮኖሚ ላይ ጥገኝነትን ለመቀነስ” በሚል ምዕራባውያን የሚያደርጉት ጥረት፣ ከቻይና የመነጠል ፅንሰ ሐሳብ እንደኾነ ተችተው፣ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

ሺ ይህን የተናገሩት፣ ከዐሥር ዓመት በፊት፥ እስያን፣ አፍሪካንና አውሮፓን፣ በየብስ እና በባሕር መንገዶች ለማገናኘት በተጀመረው የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ተነሣሽነት(“ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሺዬቲቭ”) ጉባኤ ላይ ነው፡፡

ሺ፣ ስለ ዐሥር ዓመቱ ፕሮጀክት አስመልክቶ ሲናገሩ፣ ከንድፍ አልፎ ወደ እውናዊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሊሸጋገር የቻለ ነው፤ ብለዋል፡፡

የ“ቤልት ኤንድ ሮድ” ፕሮጄክቶችን ለመደገፍ፣ የቻይና ፖሊሲ አስፈጻሚዎች፥ የቻይና ልማት ባንክ እና የቻይና ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ እያንዳንዳቸው፣ 350ቢሊዮን ዩዋን(48 ቢሊዮን ዶላር) የፋይናንስ መስጫ መስኮት እንደሚያቋቁሙ ተነግሯል፡፡

በፎረሙ፣ 97ነጥብ2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የትብብር ፕሮጀክቶች የተፈረሙ ሲኾን፣ በዋናነት ከሉላዊው ደቡብ ዓለም የተውጣጡ ከ130 በላይ ሀገራት ተወካዮች ተሳታፊ ኾነዋል።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ከተሳታፊዎች መካከል ይገኙበታል።

ፕሬዚዳንት ሺ በንግግራቸው፥ ቻይና በአንድ ወገን ማዕቀብ፣ በኢኮኖሚ ማስገደድ፣ መነጠል እና የአቅርቦት ሰንሰለት መቆራረጥ ላይ ያላትን ጽኑ የተቃውሞ አቋም በአጽንዖት ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ ተነሣሽነትና መድረኩ፣ መጀመሪያ ላይ ቻይናን ከምዕራብ አውሮፓ ጋራ ለማገናኘት ያለመ ቢኾንም፣ ታዋቂ የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች በዝግጅቱ ላይ አልተገኙም።

ኅብረቱን የወከሉት የሀንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ብቻ ነበሩ።

የሀገራት መሪዎች ቁጥርም፣ እ.ኤ.አ. በ2019 ከነበረበት 37፣ በአሁኑ መድረክ ወደ 23 ዝቅ እንዳለ ተመልክቷል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG