ቻይና ከቡድን ሰባት በሚመራው ዓለም አቀፍ የመሰረተ ልማት እቅድ ጋር የራሷን ቤልት ኤንድ ሮድ እቅድ በማጣመር ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር አብራ ለመስራት ፈቃደኛ መሆኗን አስታወቀች፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ዛሬ ሰኞ እንደተናገሩት ዩናይትድ ስቴትስ ያለችበትና ሰባቱ የበለጸጉ አገሮች ቡድን “የተሻለውን ዓለም መልሰን እንገንባ” በሚል ባለፈው ሰኔ ካወጠኑት Build Back Better World ወይም B3W ከተባለው የዓለም አቀፍ ተነሳሽነት እቅድ ጋር አብሮ ለመስራት መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡
“የተሻለውን ዓለም መልሰን እንገንባ” (B3W)የተባለው እቅድ ቻይና በታዳጊ አገሮች የመሰረተ ልማት ፍላጎት ላይ ተመስርታ የምታራምደውን ተጽእኖ ለመቋቋም ጭምር ያለመ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የB3W ተነሳሽነት ለቻይናው BRI (ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭ) አጸፋ የተነደፈ እቅድ መሆኑም በዘገባው ተገልጿል፡፡
የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር “የተሻለውን ዓለም መልሰን እንገንባ” በሚል ተነሳሽነት የሚካሄደውን እቅድ በመቀላቀል በተሻለ ጥራት ለህዝብ ጠቀሜታ የሚውሉ ምርቶች ለማቅረብ ፍላጎቱ አለን፡፡” ብለዋል፡፡
ዋንግ ይህን የተናገሩት በሻይንጋይ ስምምነት መሰረት የዛሬ 50 ዓመት በዩናይትድ ስቴትስ እና በቻይና መካከል ግንኙነቱ የተመሰረተበትን እለት በሚያከብረው ዝግጅት ላይ መሆኑን ተዘግቧል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዩናይትድ ስቴትስ በቻይናው የቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክትም ሆነ በዓለም አቀፍ የልማት ተነሳሽነት ለመሳተፍ ከፈለገች በሩ ክፍት መሆኑን ተናገረዋል፡፡ የቻይናው ፕሬዚዳንት ባለፈው መስከረም ሁሉም አገሮች ለዘላቂ እድገት አብረው እንዲሰሩ ባሰሙት ጥሪ ዢ ይህንኑ መግለጻቸውንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ዋንግ ባስተላለፉት ማሳሰቢያቸው “ዋሽንግተን በእስያ ፓስፊክ ጉዳይም ላይ ቀጣውን የግጭትና የፍጥጫ ከምታደርገው ይልቅ ቤተሰባዊ፣ ግልጽነትና አካታችነት፣ እንዲሁም ፈጠራና እድገት ብሎም ግንኙነት የዳበረበ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበት ቀጠና እንድታደርገው” አሳስበዋል፡፡
የሻንጋይ ስምምነት በፕሬዚዳንት ኒክሰን ዘመን በቻይናና ዩናትድ ስቴትስ መካከል ለዓመታት የኖረውን መነጣጠል አስቀርቶ ወደ ጋራ ትብብር ያመጣቸው መሆኑን ተመልክቷል፡፡
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በንግግራቸው ዩናይትድ ስቴትስ የታይዋንን ነጻ አገርነት መደገፏን እንድትተው አሳስበው፣ ራስ ገዝ የሆነቸው ደሴት የቻይና አካል መሆንዋን በድጋሚ አመልክተዋል፡፡