ከቻይና በሚገቡ ሸቀጦች ምክንያት የአሜሪካ አዲስ ኢንዱስትሪዎች ሲከስሙ ዋሽንግተን ማየት እንደማትሻ የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስትር ዛሬ ሰኞ ቻይና ውስጥ ተናግረዋል።
በቻይና የአራት ቀናት ጉብኝት ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስትሯ ጀኔት የለን፣ የተትረፈረፈ ምርት ወደ አሜሪካ የሚልኩ ኢንዱስትሪዎቿ ላይ ቤጂንግ ቁጥጥር እንድታደርግ ጠይቀዋል።
በእአአ 2000 መጀመሪያዎቹ ላይ ከቻይና በሚገቡ ሸቀጦች ምክንያት 2ሚሊዮን የፋብሪካ ሠራተኞች ሥራቸው ያጡበት ሁኔታ ሲደገም ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ማየት እንደማይሹ ጀኔት የለን በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
በዘጠኝ ወር ውስጥ ለሁለተኛ ግዜ ቻይና የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሯ፣ በቻይና ያለው የኢንዱስትሪ ዕድገት የሃገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላትም ያለፈ ምርት የሚያመርት ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ውጪ በሚላከው ሸቀጥ ምክንያት በአሜሪካና ሌሎችም ሃገራት የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች አደጋ ላይ ወድቀዋል ብለዋል።
አዲስ የተቋቋመውና የንግድ ልውውጥን የሚመለከተው የጋራ መድረክ፣ የተረፈ ምርቱን ጉዳይ በተመለከተ እንደሚወያይና ችግሩንም ለማስወገድ እንደሚሞክር የተናገሩት የገንዘብ ሚኒስትሯ፣ መፍትሄ ላይ ለመድርስ ግን ግዜ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም