በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቻይና ዩናይትድ ስቴትስን በዓለም ንግድ ድርጅት ከሰሰች


ፎቶ ፋይል፦ በዋረን የሚገኘው የኡልቲየም ሴል ፋብሪካ ኦሃዮ እአአ ነሃሴ 7/2023
ፎቶ ፋይል፦ በዋረን የሚገኘው የኡልቲየም ሴል ፋብሪካ ኦሃዮ እአአ ነሃሴ 7/2023

ዩናይትድ ስቴትስን "አድሎአዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ድጎማ ታካሂዳለች" ስትል የከሰሰቻት ቻይና ዛሬ በዓለም ንግድ ድርጅት ሙግት ጀምራለች፡፡

እአአ በ2022 በወጣው የዋጋ ግሽበት ቅነሳ ሕግ መሰረት፣ ከዚህ ዓመት ጀምሮ፣ በቻይና፣ ሩሲያና ሰሜን ኮሪያ ወይም በኢራን አምራቾች የተሠሩ የባትሪ ክፍሎች ያሏቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የገዙ ሰዎች ከ$3750 እስከ $7500 የሚደርሰውን የቀረጥ ተመላሽ (ድጎማ) ማግኘት አይችሉም፡፡

በዓለም ንግድ ድርጅት የቻይና ቋሚ ልዑክ ፖሊሲዎቹ “ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት በሚል ሽፋን የወጡ ነገር ግን በዩናይትድ ስቴትስ የተመረቱ ዕቃዎችን በመግዛት ወይም ከተወሰኑ ክልሎች በሚገቡ እቃዎች አጠቃቀም ላይ የተመሰረቱ ናቸው” ብለዋል፡፡

የቻይና የንግድ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በበኩላቸው ዋሽንግተን "አድሎአዊ የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎችን በፍጥነት እንድታስተካክል እና የዓለምን ኢንዱስትሪ መረጋጋት እና የአዳዲስ የኃይል ማመንጫ ተሽከርካሪዎችን አቅርቦት ሰንሰለት እንድትጠብቅ" ቤጂንግ ታሳስባለች ብለዋል።

የንግድ ሚኒስቴሩ በመግለጫው “የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች (EV) ድጎማ ክልከላው የቻይናን ምርቶች ያገለለ ቢሆንም፣ ገበያ ላይ ባለው የዓለም አቀፍ አቅርቦት ሰንሰለት እና ፍትሃዊ ውድድር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል” ብሏል።

ቻይና በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በተሽከርካሪ ላኪነት ከጃፓን ቀዳሚ ሆናለች።

የጉምሩክ ቢሮዋ መረጃ እንደሚያሳየው እ አ አ ባለፈው 2023 ብቻ ቻይና 5ነጥብ 22 ሚሊዮን መኪኖችን ወደ ውጭ የላከች ሲሆን አንድ ሦስተኛው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ናቸው ።

እአአ ከጥር 1 ጀምሮ ተግባራዊ የሆኑት አዲሶቹ የዩናይትድ ስቴትስ ሕጎች፣ አሜሪካ ውስጥ ከሚሸጡ ከ50 በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ዓይነቶች ውስጥ፣ ለቀረጥ ድጎማው ብቁ የሚሆኑት 13ቱ ብቻ ናቸው።

በ2023 ከ20 የሚበልጡ የተለያዩ ስሪት (ሞዴሎች) ያላቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለድጎማው ብቁ ነበሩ።

በዚህ የተነሳ የመኪና አምራቾች ለድጎማው ብቁ የሚያደርጋቸው መለዋወጫ እቃ ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

ከዚህኛው የቻይና ቅሬታ አስቀድሞ ሁለቱ ሀገሮች በታሪፍ እና የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያ ቲክ ቶክ በብሔራዊ ደህንነት ስጋት ምክንያት ከቻይና እናት ኩባንያው እንዲወጣ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት በቀረበው ሕግ ምክንያት በቅርቡ ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG