ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ጥረት እያደረገች ያለችው ቻይና ለአህጉሪቱ ልማት ማፋጠኛ የሚውል ስድሳ ቢሊዮን ($60) ዶላር በብድርና በዕርዳታ መልክ ልትሰጥ መሆኑ ታወቀ።
የቻይና ፕሬዚደንት ዚ ጂንፒንግ (Xi Jinping) የተመደበውን የርዳታና የብድር ገንዘብ ዛሬ ዓርብ ጆሃንስበርግ ውስጥ በተከፈተው የቻይናና አፍሪካ ትብብር የመሪዎች ጉባዔ ላይ ይፋ አድርገዋል።
ኣፍሪካ የአፍሪካ ህዝብ መሆኑዋን ችግሮችዋ መፈታት ያለባቸው በራስዋ ህዝብ መሆኑን ቻይና አጥብቃ ታምናለች በማለት በአህጉሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮች አንገባም በማለት የተናገሩት የቻይናው ፕሬዚደንት ዚ ጂንፒንግ ሀገራቸው የምትከተለውን በአፍሪካ የፖለቲካ ጉዳዮች ጣልቃ ያለመግባት ፖሊሲ ደግመው አሰምተዋል።
ምዕራባውያን መንግሥታት ቻይና በአፍሪካ ለንግዱዋና ለጥሬ ሃብቱዋ እንጂ በአህጉሪቱ ለሚካሄዱት ጦርነቶች እና የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ደንታ የላትም በማለት ይወነጅላሉ።
የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የዚምባቡዌው ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ባደረጉት ንግግር የቻይናውን ፕሬዚደንት “እርስዎ ለአፍሪካ እያደረጉ ያሉት የቀድሞ ቅኝ ገዢዎቹዋ ሊያደርጉ ይገባ የነበረውን ነው “ በማለት አሞግሰዋቸዋል።
እርስዎ ለአፍሪካ እያደረጉ ያሉት የቀድሞ ቅኝ ገዢዎቹዋ ሊያደርጉ ይገባ የነበረውን ነውፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ለቻይና ፕሬዚደንት በአፍሪካ ትብብር የመሪዎች ጉባዔ ያደረጉት ንግግር ላይ የሰጡት መልእክት
የፕሬዚደንት ሙጋቤ መንግሥት የቻይናው መሪ ሃራሬን ማክሰኞ ዕለት ሲጎበኙ የተለያዩ የምጣኔ ሃብት ውሎች ተፈራርሙዋል።
ቻይና ለአፍሪካ የመደበችው ገንዘብ አምስት ቢሊዮን ዶላሩ ከወለድ ነጻ ብድር ፡ ሰላሳ አምስት ቢሊዮን ዶላር ለተለያዩ የወጭ ንግድ እና ሌሎችም ብድሮች የሚውል መሆኑን ፕሬዚደንት ዚ ጂንፒንግ አስታውቀዋል። ዘገባውን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያዳምጡ።