የቻይና ባለሥልጣናት፣ በርካታ የእስልምና ተከታዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚገኙ መስጂዶችን ቁጥር እየቀነሱ ነው፤ ሲል፣ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን ሂዩማን ራይትስ ዋች ዐዲስ ያወጣው ዘገባ አመለከተ።
ሂዩማን ራይትስ ዋች፣ እ.ኤ.አ ኅዳር 22 ባወጣው ዘገባው፣ የቻይና መንግሥት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ “መስጂዶችን የማጠናከር ዘመቻ” በሚል፣ በመላው ቻይና የሚገኙ መስጂዶችን፣ ስልታዊ በኾነ መንገድ በማፍረስ፣ በመቀየር ወይም በመዝጋት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
ተንታኞች እና ተሟጋቾች፣ ዘመቻው፥ መንግሥት፣ አናሳ በኾኑ ሃይማኖቶች ላይ ያለውን ቁጥጥር በማጠናከር፣ የእስልምናን አሠራር እና ግንኙነት ለመገደብ ያለመ ነው፤ ይላሉ።
የሂዩማን ራይትስ ዋች የቻይና ተጠባባቂ ዲሬክተር ማያ ዋንግ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ እንደተናገሩት፣ የቻይና መንግሥት እንደሚለው፣ “መስጂዶችን እያጠናከረ” ሳይኾን፣ “ብዙዎችን እየዘጋ ነው፤” ብለዋል፡፡
እንደ እርሳቸው እምነት፣ በቻይና ያሉ መስጂዶችን ማፍረስ ወይም መልሶ ማቋቋም፣ ቤጂንግ፣ እስልምና ቻይና ውስጥ ያለውን ህልውና ለመቀነስና ሰዎች በሃይማኖቱ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለመግታት ያለመችበት አንዱ ስልት ነው።
በቻይና፣ “እስልምና ሊጠፋ ይችላል፤” የሚለው ስጋት ቢኖርም፣ በዋሽንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ግን፣ የቤጂንግ መንግሥት፣ “የዜጎችን የእምነት ነጻነት በሕግ ይጠብቃል፤” ሲል ክሱን ተከላክሏል፡፡
የኤምባሲው ቃል አቀባይ ሊዩ ፔንግዩ፣ “ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተውጣጡ ሙስሊሞች፣ በሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች፣ ሕገጋት እና ልማዳዊ ሥርዓቶች መሠረት፣ በመስጂድ እና በሀገር ውስጥ እምነታቸውን በነጻነት ማካሔድ ይችላሉ፤” በማለት ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባዩ አክለውም፣ “የሚመለከታቸው አካላት፥ እውነታውን ማክበር፣ ጭፍን ጥላቻን መተው እና መሠረተ ቢስ ወሬዎችን ማናፈስ ማቆም አለባቸው፤” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
መድረክ / ፎረም