በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቻይና 3ሺህ ኪሎሜትር በሚረዝመው ትልቁ በረሃዋ ያካሄደችውን 'የአረንጓዴ መቀነት' ፕሮጀክት ማጠናቀቋን አስታወቀች


በዢንጂአንግ ግዛት በታክላማካን በረሃ ጫፍ ግመሎችን ሲመራ ይታያል፤ ቻይና እአአ ጥቅምት 29/2013
በዢንጂአንግ ግዛት በታክላማካን በረሃ ጫፍ ግመሎችን ሲመራ ይታያል፤ ቻይና እአአ ጥቅምት 29/2013

ቻይና በረሃማነትን እና ሀገሪቱን ለጉዳት የዳረገውን የአሸዋ አውሎ ነፋስ የመከላከል ብሔራዊ ጥረቷ አካል የሆነውን እና 46 ዓመታትን የፈጀውን፣ በትልቁ የሀገሪቱ በረሃማ ስፍራ ዛፎችን የመትከል ዘመቻ ማጠናቀቋን የመንግሥት ሚዲያዎች አስታወቁ።

ከዢንጂአንግ ግዛት በስተሰሜን ምዕራብ የተካሄደው እና "አረንጓዴ ቀበቶ" የሚል ስያሜ የተሰጠው 3 ሺህ ኪሎሜትር የሚሸፍነውን በረሃ በዛፎች የመሸፈን ዘመቻ ሐሙስ ዕለት የተጠናቀቀው፣ የመጨረሻው 100 ሜትር ላይ የዛፍ ተከላ ከተካሄደ በኋላ ነው።

በረሃውን አረንጓዴ ለማድረግ የተደረገው ጥረት የተጀመረው፣ እ.አ.አ በ1978 "የሦስቱ-ሰሜን መጠለያ" ወይም በተለምዶ "ታላቁ አረንጓዴ ግርግዳ" ተብሎ በሚጠራው ፕሮጀክት ነው። ከዛን ጊዜ ጀምሮም ከ30 ሚሊዮን ሄክታር በላይ በሚሆን የበርሃው ክፍል ዛፎች ተተክለዋል።

ደረቅ በነበረው ሰሜን ምዕራብ አካባቢ የተካሄደው ይህ የዛፍ ተከላም፣ ባለፈው አመት መጨረሻ ቻይና አጠቃላይ የደን ሽፋኗን እ.አ.አ በ1949 ከነበረው 10 ከመቶ ወደ፤ ከ25 በመቶ በላይ እንድታሳድግ አስችሏታል።

ሆኖም ተቺዎች፣ ዛፎቹ የመፅደቅ እድላቸው በጣም ዝቅተኛ መሆኑንና በተደጋጋሚ በዋና ከተማዋ ቤጂንግ የሚደርሰውን የአሸዋ አውሎ ነፋስ አደጋን በመቀነስ ረገድ ውጤታማ አለመሆናቸውን ይገልጻሉ።

የዚንጂያንግ የደን ልማት ባለስልጣን ዡ ሊዶንግ ሰኞ እለት በቤጂንግ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ግን፣ ቻይና በረሃማነት ለመከላከል በታክላማካን ዙሪያ እፅዋትን እና ዛፎችን መትከሏን ትቀጥላለች ሲሉ ተናግረዋል።

ቻይና ዛፎችን የመትከል ጥረቶችን ብታደርግም ከአጠቃላይ የመሬቷ ክፍል 26.8 ከመቶ የሚሆነው አሁንም “በረሃማ” መሆኑን ከሀገሪቱ የደን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ሆኖም ከአስር አመት በፊት ከነበረው 27.2 በመቶ አሃዝ ጋር ሲነፃፀር፣ በረሃማነቱ በመጠኑ ዝቅ ማለቱ ተመልክቷል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG