በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማቷ ዘርን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ላይ የቀረቡትን ትችቶች አጣጣለች


ቻይና የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና አሁን የገዥው ኮሙዩኒስት ፓርቲ የውጭ ጉዳዮች ኮሚሽንን የሚመሩት ዋንግ ዪ
ቻይና የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና አሁን የገዥው ኮሙዩኒስት ፓርቲ የውጭ ጉዳዮች ኮሚሽንን የሚመሩት ዋንግ ዪ

ቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማቷ “ምዕራባውያን፣ በቻይናዊያን ኮሪያዊያን እና ጃፓናዊያን መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ አይችሉም” ሲሉ ዘርን ተንተርሰው በሰጡት አስተያየት ላይ የተሰነዘሩትን ትችቶች አጣጥላለች፡፡

“አሜሪካውያን ከቻይና ከደቡብ ኮሪያ እና ከጃፓን የመጡትን ሁሉንም ጎብኚዎች እንደ እስያዊያን ይወስዷቸዋል፡፡ ልዩነቶቻቸውን መለየት አይችሉም፣ ይህ በአውሮፓም ተመሳሳይ ነው” በማለት አስተያየት የሰጡት የቻይና የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና አሁን የገዥው ኮሙዩኒስት ፓርቲ የውጭ ጉዳዮች ኮሚሽንን የሚመሩት ዋንግ ዪ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

ዋንግ በአስተያየታቸው “ጸጉርህን የቱንም ያህል ቢጫ ብትቀባው፣ ወይንም የቱን ያህል አፍንጫህን ወደ ሰልካካነት ብትቀይረው መቸም ቢሆን ወደ አውሮፓዊነትም ሆነ አሜሪካዊነት አትቀየርም፣ መቸም ቢሆን ወደ ምዕራባዊነት አትቀየርም፡፡”ሲሉ መናገራቸውም ተዘግቧል፡፡

ዋንግ ይህን የተናገሩት በሰሜናዊ ቺንግዳኦ ከተማ በተካሄደ የሶስትዮሽ ጉባኤ ላይ ነው፡፡

ዋንግ በንግግራቸው “ቻይና ጃፓን እና ኮሪያ እጅ ለእጅ ተያይዘን ብንተባበር፣ የሶስቱን አገሮቻችንን ፍላጎት ብቻ የሚያስማማ ብቻ አይሆንም፣ የህዝቦቻችንን ምኞት የሚያስማማ ይሆናል፣ በአንድነት መበልጸግ ምስራቅ እስያን ዳግም እንድታብብ ማድረግና ዓለምን ማበልጸግ እንችላለን” ብለዋል፡፡

የዋንግ አስተያየት በተለይም ኢንተርኔት ላይ ያሉ ምሁራንን አስተያየትና ትችት መሳብ የቻለው ወዲያውኑ እንደነበር ተነግሯል፡፡

የሶስቱን ሀገራት ትብብር አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩት ዋንግ፣ "ከአካባቢው ውጪ ያሉ አንዳንድ ትላልቅ ሀገራት የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶችን ሆን ብለው ያጋንናሉ ፣ ልዩ ልዩ ትንንሽ ቡድኖችና ስብስቦችን በመፍጠር ትብብርን በግጭት፣ አንድነትን በመከፋፈል ለመተካት ይጥራሉ" ብለዋል።

ይህ አስተያየት በግልጽ የቻይና ዋነኛ ተቃናቃኝ የሆነችውና የበላይነት ለመያዝ ትሞክራለች ብላ ቻይና ዘወትር የምትከሳትን ዩናይትድ ስቴትስን የሚመለከት አስተያየት መሆኑ ተነግሯል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ አምባገነንና የአንድ ፓርቲ ስርዓት ካላት ቻይና በተቃራኒ፣ ነጻ ማህበረሰብና የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ካላቸው ሁለቱ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ጋር የደህንነት ትብብር እንዳላት ይታወቃል፡፡

በምስራቅ እስያ የቻይና የቅርብ ወዳጅ የሆኑት አገሮች ሰሜን ኮሪያና ሩሲያ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

“ይህ መልዕክት በጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ምድር ላይ ጥሩ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ በርግጥ ዋንግ በትክክል አገራዊ ፍላጎቶች ከመልክ ገጽታ ያነሰ አስፈላጊ ናቸው ብለው ያስባሉ?” ሲሉ ትዊት ባደረጉት ጽሁፍ የጠየቁት በእስያ የዩናይትድ ስቴትስ የጆርጅ ማርሻል ፈንድ ዳይሬክተር ቦኔ ግላሰር ናቸው።

“ጃፓኖችና ኮሪያውያን አሜሪካውያን አትሆኑም ሲሉ” ዋንግ ዪ የተናገሩትን የተቹት በዩናይትድ ስቴትስ የሄሪቴጅ ፋውንዴሽን የእስያ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር፣ ጄፍ ኤም ስሚዝ ደግሞ፣ “ጃፓኖች እና ኮሪያውያን አሜሪካዊ የሚሆኑት በየቀኑ ነው” ብለዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ዜግነትን የወሰዱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቻይናውያን፣ጃፓኖችና የኮሪያ ዝርያ ያላቸው መኖራቸው ይታወቃል፡፡

XS
SM
MD
LG