በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቻይና የዩክሬንን ትችት አስተባበለች


የስዊዘርላንድ ባንዲራ ከቡርገንስቶክ ሪዞርት ፊት ለፊት ይታያል ስዊዘርላንድ እአአ ግንቦት 28 ቀን 2024
የስዊዘርላንድ ባንዲራ ከቡርገንስቶክ ሪዞርት ፊት ለፊት ይታያል ስዊዘርላንድ እአአ ግንቦት 28 ቀን 2024

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ፣ በዚህ ሳምንት በስዊዘርላንድ በሚካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ ላይ “ቻይና ሀገራት እንዳይሳተፉ ጫና እያሳደረች ነው” በሚል ያቀረቡትን ትችት ቻይና አስተባበለች።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ፣ ማኦ ኒንግ፣ ባለፈው ሰኞ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ቤጂንግ የሰላም ንግግሮችን ለማራመድ ያላት ቁርጠኝነት ገልጸው “ጉባኤው ለግጭት ጎራ መፍጠሪያ እንደማይውል ተስፋ ታደርጋለች” ብለዋል፡፡

ቃል አቀባዩ አክለው፣ “በጉባዔው ላይ አለመገኘት ማለት ሰላምን አለመደገፍ ማለት አይደለም” ብለዋል።

ማኦ ኒንግ አያይዘው “ቻይና እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም፣ ግጭቱን አላቀጣጠለችም ወይም በግጭቱ አላተረፈችም፡፡ ይልቁንም ሩሲያና ዩክሬንን ጨምሮ በቡዙ ወገኖች የተመሰገነው የተኩስ አቁም እንዲኖር ያላማቋረጥ ሠርተናል” ብለዋል።

ለዩክሬን ፕሬዚድናት ዜለነስኪ ምላሽ ከመስጠት በተጨማሪ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ የቻይናን የሰላም እቅድ አስተዋውቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ ባላፈው ማክሰኞ ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በመሆን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “ዓለም ለዩክሬኑ ቀውስ አሁን የሚፈልገው ይበልጥ ተጨባጭ፣ ሚዛናዊ፣ አዎንታዊና ገንቢ የሆኑ ድምጾችን እንደሆነ ቻይና ታምናለች” ብለዋል፡፡

ለዩክሬን ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሄ መስጠትን በተመለከተ ቻይና እና ብራዚል በጋራ ያወጡትን ስድስት የጋራ ነጥቦች በማጉላት የቻይናን የሰላም እቅድ ይፋ አድርገዋል። ዋንግ ዪ አክለው በአንድ ሳምንት ውስጥ ከአምስት አህጉራት የተውጣጡ 45 ሀገራት ለሰላም ዕቅዱ አወንታዊ ምላሽ እንደሰጡ ጠቅሰዋል።

ተንታኞች ቻይና የስዊዘርላንድን ስብሰባ ለመቀላቀል ፈቃደኛ አለመሆኗ፣ ሩሲያን በመደገፏ የሚቀርብባትን ትችትን ለማስወገድ ነው ያሉ ሲሆን፣ ዩክሬን በቻይና ገለልተኝነት አቋም ያላት እምነት እየቀነሰ መምጣቱን አመልክተዋል። የቻይና እና ሩሲያ በጉባኤው ላይ አለመሳተፍ ጉባኤው የሚኖረውን አንድምታ እንደሚቀንሰውም ተንታኞቹ ጨምረው ገልጸዋል።

ቻይና ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ በጉባኤው ላይ የሚሳተፉ ምዕራባውን የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ስላላቸው ቅንነት ጥርጣሬ ያላት መሆኑ ተገልጿል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG