በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቻይና በአፍሪቃ የአረንጓዴ ኃይል ላይ ያላት የመዋዕለ ነዋይ ዕቅድ


ቻይና በአፍሪቃ የአረንጓዴ ኃይል ላይ ያላት የመዋዕለ ነዋይ ዕቅድ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:02 0:00

ቻይና በአፍሪቃ የአረንጓዴ ኃይል ላይ ያላት የመዋዕለ ነዋይ ዕቅድ

ከአፍሪካ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኘው ከፊሉ ብቻ ነው። ቻይና ለመፍታት የምታስበው፣ ይህን ችግር ነው። ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እ.አ.አ. በ2021፣ ተጨማሪ የድንጋይ ከሰል ማምረቻዎችን በውጭ ሀገራት ላለመገንባት ቃል ከገቡ በኋላ፣ ትኩረታቸው በነፋስ እና በፀሐይ ኃይል በሚሠሩ የኃይል ማመንጫዎች ላይ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ መኾኑን ይናገራሉ።

ናሚቢያ በሚገኘው የነፋስ ኃይል ማመንጫ እና በዚምባብዌው ግዙፉ የካሪባ ግድብ ላይ የተሠራው ተንሳፋፊ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ፣ የቻይና ኩባንያዎች፥ በያዝነው ዓመት መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ከሚያስቡቧቸው ዐዲሶቹ የአፍሪካ አረንጓዴ የኃይል ምንጭ ፕሮጀክቶች ውስጥ ናቸው።

ቶኒ ቲዩ፣ በአፍሪካ ከካርቦን ብክለት ነጻ ኃይል የሚያመነጨው “Renewables in Africa” የተሰኘው ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ናቸው። ቻይና፣ አፍሪቃ ላይ መዋዕለ ነዋይ ፈሰስ የማድረጓ አዎንታዊ ፋይዳ ነው የሚታያቸው።

“የኤሌክትሪክ አቅርቦት 54 በመቶ ብቻ በኾነባት አፍሪቃ ያለውን ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት እጥረት የሚያሳይ በቅጡ የተደራጀ መረጃ አለ። በአንጻሩም፣ እያደገ የመጣው የምጣኔ ሃብቷ፣ አህጉሪቱ ልታስገኝ የምትችለውን ከፍ ያለ ትርፍ ሊያስገኝ የሚችል የንግድ ሥራ ዕድል ያሳያል።”

እ.አ.አ. በ2050 ሙቀት አማቂ የጋዝ ልቀትን ወደ ዜሮ ለማውረድ የሚያልመው የፓሪስ ስምምነት ግብ ለስኬት ይበቃ ዘንድ፣ “ዓለም አቀፍ ጥረትን ይጠይቃል፤” ሲሉ የለንደኑ የኢኮኖሚክስ እና የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ቤት ባልደረባ ሊየ ቢየን ይናገራሉ።

“በዓለም አቀፍም ኾነ በአህጉር ደረጃ ‘ኔት ዜሮ’ ወደተባለውና ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ በመቀነስ ወደ ዜሮ የማስጠጋት ሽግግር ለማሳካት፣ የፋይናንስ ምንጭ ካላቸው ከሁሉም አገሮች የተሰባሰበ ጥረት ይጠይቃል።”

ዩናይትድ ስቴትስም በአፍሪካ፣ በታዳሽ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ መዋዕለ ነዋይ እያፈሰሰች ብትኾንም፣ የፀሐይ እና የነፋስ ኃይል ማመንጫዎችን በመሥራት በዓለም ትልቋ አገር ቻይና ናት። ኩባንያዎቿም በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የታዳሽ ኃይል ማመንጫ መሣሪያዎችን ቢገነቡም፣ ታዳሽነት የሌለውን መደበኛ የኃይል ምንጭ በማምረት ዐቅም ግንባታው ረገድ ከየትኛውም አገር ይበልጥ መሥራታቸው አልቀረም፤” የሚሉት ኮበስ ቫን ስታደን፣ “The China Global South Project” የተባለውና ቻይና በአፍሪቃ የምታካሒዳቸውን ሥራዎች የሚከታተል፣ ለትርፍ ያልቆመ የዘርፈ ብዙ የብዙኃን መገናኛ ተቋም ባልደረባ ናቸው።

“ዢ ጂንፒንግ፣ ለቻይና የነዳጅ እና የድንጋይ ከሰል አቅርቦቶችን ለማስጠበቅ ተግተው የሚሠሩትን ያህል፣ ታዳሽ የኃይል ምንጮችንም ለማስፋት እና ለማሳደግ የቻሉትን ያህል ጠንክረው በመሥራት ላይ በመኾናቸው፣ ከዚያም አንጻር የነገሩን ውስብስብ ገጽታ ልብ ማለት ያስፈልጋል።”

ለምሳሌ ያህል፣ የቻይናው ናሽናል ኦፍሾር ኦይል ኮርፖሬሽንና የፈረንሳዩ ኩባንያ ቶታል ኢነርጂ፣ በምሥራቅ አፍሪካ አወዛጋቢ በኾነ የድፍድፍ ነዳጅ ማስተላለፊያ መሥመር ግንባታ ፕሮጀክት ላይ መዋዕለ ነዋይ ያፈስሳሉ።

ተቺዎቻቸው፣ ፕሮጀክቱ፥ ሰዎችን ከቀዬአቸው ከማፈናቀልና የተፈጥሮ አካባቢ ላይ ጉዳት ከማድረስ ጋራ የተያያዙ ስጋቶችን የሚደቅን ነው፤ ሲሉ፣ ደጋፊዎቻቸው በአንጻሩ፣ በጣም አስፈላጊ የኾነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ አህጉሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ያመጣሉ፤ ባይ ናቸው።

ደቡብ አፍሪቃ በበኩሏ፣ በድንጋይ ከሰል ማሠራጫ ጣቢያዎቿ እርጅና እና በየዕለቱ የመብራት መቆራረጥ፣ የምጣኔ ሃብቷን እያሽመደመዱት በመምጣታቸው የኃይል ምንጭ ቀውስ ገጥሟታል።

ዐዲሱ የኤሌትሪክ ኃይል ሚኒስትር ኮሲየንትሶ ራሞኮፓ፣ የመጀመሪያ ከአደረጓቸው ርምጃዎች አንዱ፣ ባለፈው ወር ከቻይና አምባሳደር ቼን ዢያኦዶንግ ጋራ ተገናኝተው፣ ቻይና እንዴት አገራቸውን ልትረዳ እንደምትችል ለማየት ያደረጉት ምክክር ነው። የቻይናው ሂነኒ ግሩፕ፣ በደቡብ አፍሪቃ የታዳሽ ኃይልን ምንጭ ለመገንባት ዕቅድ አለው።

ቻይና በአፍሪቃ፣ በቅርቡ የገነባቻቸውና ለመገንባትም ያስተዋወቀቻቸው አብዛኛዎቹ የአረንጓዴ ኢነርጂ ፕሮጀክቶች፣ በቀደሙት ዓመታት፣ ወደብ እና የባቡር ሐዲድ ግንባታዎችን ከመሳሰሉት ግዙፉ የቤልት ኤንድ ሮድ መሠረተ ልማት ውጥኖች ጋራ ሲነጻጸሩ፣ አነስተኛ የሚሰኙ ናቸው።

ፕሬዝዳንት ዢ፣ “ትንሽ ነገር ውብ ነው” ከሚሏቸው ፕሮጀክቶች፣ አገራቸው ቤጂንግ፣ “አረንጓዴው የሐር መንገድ” እየተባለ በሚጠራው ፕሮዤ ትኩረት ለማድረግ የያዘችው ውጥን አካል ነው።

XS
SM
MD
LG