በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ደቡባዊ ካሊፎርኒያ በሚገኝ የመስሪያ ቤት ህንጻ አራት ሰዎች በጥይት ተገደሉ


ዩናይትድ ስቴትስ ደቡባዊ ካሊፎርኒያ በሚገኝ የመስሪያ ቤት ህንጻ አራት ሰዎች በጥይት ተገደሉ። ከተገደሉት መካከል አንዱ ልጅ መሆኑ ተገልጿል።

በሀገሪቱ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንደዚህ ያለ የጅምላ ግድያ ሲፈጸም የትናንቱ ሦስተኛ መሆኑ ተገልጿል።

ከሎስ አንጀለስ በስተደቡብ ምስራቅ ባለችው ኦሬንጅ ከተማ ተኩስ የከፈተውአጥቂው ራሱናአንድ ሌላ ሰው በጽኑ መቁሰላቸው ታውቋል።

ትናንት አስራ አንድ ሰዓት ተኩል ላይ ፖሊሶች ተጠርተው ሲደርሱ ባለአምስት ፎቁ ህንጻ ላይ ሲተኮስ እንደነበር የተናገረው የከተማዋ ፖሊስ፣ ተጠርጣሪ አጥቂው ወደሆስፒታል መወሰዱን አመልክቷል።

አጥቂ የቆሰለው በራሱ መሳሪያ ይሁን ወይም ፕሊስ ተኩሶበት እንደሆን አልተገለጸም።

ፖሊሶች ከተገደሉት መካከል አንድ ህጻን እና አንዲት ሴት እንዳሉበት ከመግለጽ በስተቀር ሌላ ዝርዝር አልሰጡም። የካሊፎርኒያ አገረ ገዢ ጋቪን ኒውሰውም በትዊተር ገጻቸው

"በዚህ ዘግናኝናልብ የሚሰብር ጥቃት ለተጎዱ ቤተሰቦች ሁሉ ሃዘናችንን እንገልጻለን" ብለዋል።

ፖሊስ ትናንት ማታ በሰጠው ቃል ጥቃቱን ምን እንዳነሳሳው መረጃ እንደሌለው ነበር ያስታውቀው። ህንጻው ደጃፍ በተለጠፉት የድርጅት ስሞች እንደሚታየው የኢንሹራንስ ኩባኒያ የቴሌፎን ማደሻን ጨምሮ የተለያዩ የግል ኩባኒያ ቢሮዎች እና የንግድ ቤቶች ያሉበት ነው።

በዩናይትድ ስቴትስ ባለፈው ሳምንት ኮሎራዶ ክፍለ ሃገር ቦልደር ከተማ በሚገኝ የምግብ እና ሸቀጣ ሸቀጥ መደብር አጥቂ ተኩስ ከፍቶ አስር ሰዎች እንደገደለ ከዚያ በአንድ ሳምንት ቀደም ብሎም በጆርጂያዋ አትላንታ ከተማ በሚገኙ የመታሻ ቤቶች ስድስት እስያ ዝርያ ያላቸው ሴቶችን ጨምሮ ስምንት ሰዎች በጥይት መገደላቸው የሚታወስ ነው።

XS
SM
MD
LG