አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ከፍተኛ የአረብ አገራት ዲፕሎማቶች ትናንት እሁድ ‘የትሪፖሊው መንግሥት የሥልጣን ዘመኑ አብቅቷል’ ያሉ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች አንሳተፍም ባሉበት ስብሰባ መገናኘታቸው ተነገረ።
ከ22ቱ የአረብ ሊግ አባል ሃገሮች አምስቱ ብቻ ናቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን በየጊዜው ወደሚካሄደው ወደዚህ የምክክር ጉባኤ የላኩት።
ይህም የጎረቤት አልጄሪያን እና ቱኒዝያን ከፍተኛ ዲፕሎማቶች እንደሚጨምር የሃገሬው የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ምስራቃዊ ሊቢያ ውስጥ የሚገኘው የአገሪቱ ፓርላማ ባለፈው ዓመት ተቀናቃኝ ጠቅላይ ሚንስትር መሾሙን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደል ሃሚድ ዲበይባህን መንግሥት ህጋዊነት ላይ ጥያቄ ያቀረበችው ግብፅ በስብሰባው ላይ አልገኝም ካሉት ውስጥ አንዷ ናት።
በንጉሳውያኑ የሚተዳደሩት ሁለቱ የባህረ ሰላጤው አገሮች ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና እንዲሁም የአረብ ሊግ ዋና ፀሃፊ አህመድ አቡልጊየትም በስብሰባው ያለመገኘታቸው ታውቋል።
ትሪፖሊ የሚገኘው የሊቢያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናጃላ ማንጉሽ በበኩላቸው በቴሌቭዥን ባሰሙት ንግግር የአረብ አገሮች በየተራ የሚመሩትን የአረብ ሊግ ማሕበር ለመምራት ሊቢያ ያሏትን መብቶች ሙሉ በሙሉ እንደምትጠቀም ተናግረዋል።