በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሐረርን ውኃ ጥም እና የተማሪዎች ችግር ለመቁረጥ የተወላጆች ማኅበሩ እየተንቀሳቀሰ ነው


የሐረርን ውኃ ጥም እና የተማሪዎች ችግር ለመቁረጥ የተወላጆች ማኅበሩ እየተንቀሳቀሰ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:28 0:00

የሐረርን ውኃ ጥም እና የተማሪዎች ችግር ለመቁረጥ የተወላጆች ማኅበሩ እየተንቀሳቀሰ ነው

በዩናይትድ ስቴትስ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀሰው “ደንበር የለሽ የሐረር ልጆች ማኅበር” ፣ በሐረር ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕፃናትን፣ በትምህርት ቁሳቁሶች ሲረዳ ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ ገባሬ ሠናይ ተቋሙ፣ የሐረር ከተማ ነዋሪ አብሮት የከረመውን የውኃ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ፕሮጀክት ጀምሯል። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ፣ እስከ 50 በመቶ የሚደርሰው የከተማው ነዋሪ፣ በየቤቱ ንጹሕ ውኃ ሊያገኝ እንደሚችልም፣ የማኅበሩ የቦርድ አባል አቶ ዮሐንስ ደምሴ ተናግረዋል።

እ.አ.አ በ1998፣ በአሜሪካ ሲያትል ከተማ ነዋሪ በኾኑ አምስት የሐረር ተወላጆች፣ በሐረር ከተማ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን ድጋፍ ለማድረግ አስበው “የሐረር ልጆች ማኅበር”ን መሠረቱ። በወቅቱ ለሐረር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ኮምፒውተሮችንና የማተሚያ ማሽኖችን መላክ ቢችሉም፣ ማኅበሩ ብዙ ሳይቆይ ተበተነ።

የሐረር የትምህርት ተቋማት እና ተማሪዎች፣ ዛሬም ያሉባቸውን ሰፊ ችግሮች ያስተዋሉት የአካባቢው ተወላጆች፣ የተቀናጀ ድጋፍ ለማድረግ አልመው፣ ከአራት ዓመት በፊት የማኅበሩን የቀድሞ አባላት ዳግም በማሰባሰብ “ደንበር የለሽ የሐረር ልጆች ማኅበርን” መሠረቱ፤ በትምህርት ቁሳቁሶች መደገፋቸውንም ቀጠሉ። በዚኽ መሀከል፣ ለሐረር ነዋሪ ነባር የኾነው የውኃ እጥረት፣ በልጆች ትምህርት ላይ እያሳደረ ያለውን ችግር ማስተዋል እንደጀመሩ፣ የተቋሙ የቦርድ አባል አቶ ዮሐንስ ደምሴ ይገልጻሉ።

የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር፣ ከዐሥር ዓመታት በላይ ሐረርን ለጥም እየዳረጋት ይገኛል፡፡ አለ የሚባለውም የውኃ አቅርቦት፣ ጊዜያዊ እንጂ አስተማማኝ አይደለም፡፡ ለአንድ ወይም ለሁለት ሳምንት፣ አንዳንዴም ለወር ያህል ውሃ ሊጠፋ ይችላል። ይህ ዐይነቱ የከፋ እጥረት፣ በትምህርት አሰጣጥ እና አቀባበል ረገድ በተማሪዎች ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ ለማስወገድ፣ የደንበር የለሽ የሐረር ልጆች ማኅበር አባላት፣ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ጉድጓዶችን በማስቆፈር፣ ለአጠቃላይ ማኅበረሰቡ የከርሰ ምድር ውኃን ለማዳረስ ጥረት እያደረጉ እንደኾኑ፣ አቶ ዮሐንስ ያብራራሉ።

ማኅበሩ፣ ከሐረር ከተማ አስተዳደር ጋራ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም፣ በጥናቱ መሠረት በተመረጡ አራት ቦታዎች ላይ የውኃ ጉድጓዶችን በማስቆፈር ላይ ይገኛል። ቁፋሮው ሲጠናቀቅም፣ ለረጅም ጊዜ በሐረር የኖረውን የውኃ ችግር እንደሚፈታ ይጠበቃል።

ማኅበሩ፣ በዐዲስ መልኩ ከጀመረው የከርሰ ምድር የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ፕሮጀክት ጋራ፣ ከጥንቱም የተቋቋመበትን፣ በትምህርት ቁሳቁሶች የመርዳት እና እውቀትን የማሸጋገር ዓላማው እንደቀጠለ ነው። በተቋሙ ተጠቃሚ ከኾኑ ትምህርት ቤቶች መካከል፣ የሐረር ሁለተኛ ምደባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይገኝበታል።

የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ወይዘሮ ዙፋን እንደሚሉት፣ በሐረር፣ በኑሮ ደረጃ ከዝቅተኛ ቤተሰቦች የመጡ ተማሪዎች በብዛት በሚማሩበት በዚኽ ትምህርት ቤት፣ 250 የሚደርሱ ተማሪዎች ተቋሙ በሚያደርገው ድጋፍ ተጠቃሚ ኾነዋል። ተማሪዎቹ ብቻ ሳይኾኑ፣ መምህራኑ እና የትምህርት ቤቱ ሠራተኞችም፣ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

“ደንበር የለሽ የሐረር ልጆች ማኅበር” ከትምህርት ቤቶች ድጋፉ በመለስ፣ በግለሰብ ደረጃም በርካታ ችግረኛ ሕፃናትን ይረዳል፤ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውንም ያሳክማል። አቶ ዮሐንስ ታዲያ፣ ተቋሙ ለትምህርት ቤቶች በሚያደርገው እገዛ፣ የበርካቶች ተስፋ መታደሱን፣ በተለይ ደግሞ በውኃ ቁፋሮው፣ የብዙዎችን ሕይወት እንደቀየረ ያመለክታሉ፡፡

በርካታ ተከታታዮቻቸው፣ “ለምን የሐረርን ልጆች ብቻ?” እያሉ እንደሚጠይቋቸው የጠቀሱት አቶ ዮሐንስ፣ ምክንያቱ ከዐቅም ውሱንነት ጋራ ብቻ የተያያዘ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ የማኅበሩ የወደፊት ዓላማ፣ የመላዋ ኢትዮጵያ ተማሪዎችን ማገዝ እና ትምህርትን ማስፋፋት እንደኾነም አመልክተዋል። ለዚኽም፣ ዐቅሙ እና በጎ ፈቃዱ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲተባበር፣ ተቋሙ በሚያደርጋቸው የገንዘብ ማሰባሰቢያዎችም ላይ እንዲሳተፍ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG