በወንጀል ተጠርጥረው ክሥ ቀርቦባቸው የነበሩ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮችን ክሥ፣ ማቋረጡን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ።
“በወንጀል ተጠርጥረው ክሥ ቀርቦባቸው የነበሩ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮችን ክሥ በማቋረጥ፣ ጉዳያቸው በቀጣይ በሽግግር ፍትሕ ማኅቀፍ እንዲታይ ማድረግ አስፈላጊ ኾኖ ተገኝቷል፤” ሲል የፍትሕ ሚኒስቴር ከሰዓታት በፊት በፌስቡክ ገጹ ላይ በአሰፈረው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ለኹለት ዓመታት ከተካሔደው ጦርነት ጋራ የተያያዙ ወንጀሎች፣ በሽግግር ፍትሕ ይታያሉ፤ ብሏል መግለጫው፡፡
“በፌዴራል መንግሥት እና በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) መሀከል በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሠረት፣ ከግጭቱ ጋራ ተያያዥ የኾኑ ወንጀሎች ተጠያቂነትን በተመለከተ ያለውን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ታሳቢ በአደረገ መልኩ፣ በሽግግር ፍትሕ ማኅቀፍ ሊታዩ እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል፤” ሲል አክሏል የሚኒስቴሩ መግለጫ፡፡
“በክርክር ሒደት ላይ ይገኙ የነበሩ የወንጀል ክሦች፣ በዐዋጅ 943/2008 አንቀጽ 6(3)(ሠ) መሠረት የተነሡ መኾኑን እናሳውቃለን፤” ሲል ሚኒስቴሩ መግለጫውን ደምድሟል፡፡