በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሴናተሩ በአሜሪካ የሠለጠኑ ኀይሎችን በሣህል አካባቢ መፈንቅለ መንግሥት ከሰሱ


ፎቶ ፋይል፦ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሴናተር ቤን ካርዲን
ፎቶ ፋይል፦ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሴናተር ቤን ካርዲን

በሣህል አካባቢ ሀገራት መፈንቅለ መንግሥት የፈጸሙት፣ በአሜሪካ የሠለጠኑ ሚሊሺያዎች እና ወታደሮች ናቸው፤ ሲሉ፣ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሴናተር ቤን ካርዲን ከሰሱ፡፡

ሴናተሩ፣ ትላንት ማክሰኞ እንደተናገሩት፣ አሜሪካ፣ ለሣህል እና ለምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ስትሰጥ የነበረው የጸጥታ እገዛ፣ “ውጤታማ ነው ለማለት ያዳግታል፤” ሲሉ ተችተዋል፡፡

በሣህል እና በምዕራብ አፍሪካ ያለው አለመረጋጋት የሚኖረውን አንድምታ አስመልክቶ፣ የሴኔቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ፣ ትላንት አዘጋጅቶት በነበረው የውይይት መድረክ መክፈቻ ላይ የተናገሩት ሊቀ መንበሩ እና ከሜሪላንድ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ተወካዩ ሴናተር ቤን ካርዲን እንዳሉት፣ “በሣህል እና በምዕራብ አፍሪካ፣ የተሻለ ጸጥታ፣ መረጋጋት እና ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማትን በመፍጠር ረገድ፣ አሜሪካ ሠራኹ ብላ ማሳየት የምትችለው ነገር እጅግ ጥቂት ነው፤” ብለዋል፡፡

“በሣህል አካባቢ መፈንቅለ መንግሥት የፈጸሙት፣ በአሜሪካ የሠለጠኑ ሚሊሺያዎች እና ወታደሮች ናቸው፤” ሲሉም ካርዲን ከሰዋል። “የሲቪል መንግሥታትን የገለበጡት፣ እኛ ያሠለጠንናቸው ሰዎች ናቸው፤ ሐቁን መናገር አለብን፤” ሲሉም አክለዋል።

በአካባቢው የሩሲያ ቅጥር ወታደራዊ ቡድን የኾነው ቫግነር መገኘት፣ ተጨማሪ ስጋት ደቅኗል፤ ያሉት ሴናተሩ፣ የፈረንሳይ ጦር እና የተመድ ሰላም አስከባሪዎች፣ ከአካባቢው እንዲወጡ መደረጋቸው፣ ሌላ ቀውስ ሊፈጥርና ከቀውሱም በቀላሉ መውጣት አስቸጋሪ ሊኾን እንደሚችል አመልክተዋል።

“ቃላት መምረጥ ሳያስፈልገን፣ አቋማችንን ግልጽ ማድረግ አለብን። ወታደሩ፣ የሲቪል መንግሥት አስተዳደርን በጉልበት ከወሰደ፣ መፈንቅለ መንግሥት እንደኾነ በማያሻማ ቋንቋ መናገር አለብን፤” ብለዋል ሴናተር ካርዲን።

ባለፉት ሦስት ዓመታት፣ በሣህል ቀጣና እና በምዕራብ አፍሪቃ አምስት ሀገራት ላይ መፈንቅለ መንግሥት ተካሒዷል። እነርሱም፥ ማሊ፣ ጊኒ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ቻድ እና በቅርቡ ደግሞ ኒዤር ናቸው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG