በመላው ዓለም ከፍተኛ ዝና ባተረፈው በብላክ ፓንተር ፊልም የአፍሪካዋ ልብ ወለድ ንጉሣዊ ግዛት የዋካንዳ ንጉሥ ቲ ቻላን ሆኖ ባሳየው የላቀ የተዋናይነት ጥበብ ዕውቅና ያገኘው ቻድዊክ ቦዝማን ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ
ቻድዊክ በአርባ ሶስት ዓመቱ በአንጀት ካንሰር ህመም ምክንያት ህይወቱ ማለፉ ታውቋል
ቻድዊክ ቦዝማን እ አ አ ከ2016 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ስለህመሙ ይዞታ ያወቀ ቢሆንም መታመሙን በይፋ ሳይናገር በታላላቅ የሆሊዉድ ፊልሞች ስራውን ያለማቋረጥ መቀጠሉ ተገልጿል
በማህበራዊ መገናኛ ገጹ ላይ የወጣው መግለጫ ታሞም "ለሙያው በነበረው ክብር በብላክ ፓንተር ፊልም ለንጉሥ ቲቻላን ዕውን ማድረግ ነበረበት" ሲል አስቀምጦታል
ቻድዊክ ቀደም ብሎም ስመ ጥር ጥቁር አሜሪካውያን ፈርጦችን ተመስሎ በተዋናይነት ተጫውቷል ፥ ጥቁር አሜሪካዊው የቤዝቦል ተጫዋች ጃኪ ሮቢንሰንን 42 በተሰኘው ፊልም ዕውቁን ድምጻዊ ጄምስ ብራውንን ጌት ኦን አፕ በተባለው ፊልም ተጫውቶ አድናቆት አትርፏል
በቅርቡም በስፓይክ ሊ በተዘጋጀው ዳ ፋይቭ ብለድስ በተባለው ፊልም ተዋናይ ነበር