ዋሺንግተን ዲሲ —
በቻድ አዲሱን የሽግግር መንግሥት ለመግልበጥ የሚንቀሳቀሱት ሽምቅ ተዋጊዎች ወታደራዊ ሄሊኮፕተር መትተን ጥለናል፣ “ኖኩ” የምትባለውን የሰሜን ቻድ ከተማም ተቆጣጥረናል እያሉ እንደሆነ ተገለጸ።
የቻድ የለውጥ እና የአንድነት ግንባር የተባለው ታጣቂ ቡድን ያለውን በነጻ ምንጭ በኩል ለማረጋገጥ አልተቻለም።
የቡድኑ ቃል አቀባይ በሰጠው መግለጫ የጦር ሄሊኮፕተሩ በሰሜኑ የሀገሪቱ አካባቢ የቦምብ ጥቃት በማድረስ ላይ ሳለ ተዋጊዎቻችን ተኩሰው ጥለውታል ብሏል።
በሌላ በኩል ሰላማዊ ሰልፍ እንዲካሄድ በድጋሚ ጥሪ እየተደረገ ሲሆን የሽግግር ወታደራዊ መንግሥቱ ቃል አቀባይ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ከሁከት እንዲቆጠቡ አሳስቧል። ማክሰኞ ዕለት በዋና ከተማዋ ኢንጃሜና በተከሰተ ብጥብጥ ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።