ቻድ ሰሜናዊ ክፍለ ግዛት ውስጥ ባለፈው ሳምንት በወርቅ ማዕድን በሚቆፍሩ ሰዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ከአንድ መቶ የሚበልጡ ሰዎች መገደላቸውን የሀገሪቱ መንግሥት አስታወቀ።
ግጭቱ የተቀሰቀሰው ቻድን ከሊቢያ ጋር በሚያዋስናት ድንበር አቅራቢያ ሲሆን አካባቢው ካለፈቃድ የወርቅ ማዕድን ቁፋሮ የሚካሄድበት መሆኑ ተመልክቷል።
ትናንት የቻድ የመከላከያ ሚኒስትር እንዳሉት በግጭቱ ከ100 የሚበልጡ ሲገደሉ ከአርባ የሚበልጡ ቆስለዋል። የግጭቱን ምክንያት አልገለጹም። ይሁን እንጂ ባለፈው ሳምንት የቻድ የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ግጭቱ ከሊቢያ ድንበር አቋርጠው በገቡ አረቦች እና በምስራቅ ቻድ ታማ ማኅበረሰብ አባላት መካከል መሆኑን ተናግረዋል።
ግጭቱን ተከትሎ የቻድ መንግሥት ካለፈቃድ ወርቅ ማዕድን ቁፋሮ እንዳይካሄድ የከለከለ ሲሆን ነዋሪዎቹን ከአካባቢው አውጥቷል።
በሁከቱ የሽብርተኛ ወይም ሌላ የወንጀል ቡድን እጅ እንዳለበት የሚያሳይ ምንም ምልክት እንደሌለ ተገልጿል።