በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በስልጤ ዞን ከስድስት ሺሕ በላይ ሰዎች በጎርፍ መፈናቀላቸው ተገለጸ


በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስልጤ ዞን ሁለት ወረዳዎች እና በማረቆ ልዩ ወረዳ አንድ ቀበሌ ውስጥ በተከሠተ የጎርፍ አደጋ፣ ከስድስት ሺሕ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን፣ ተጎጂዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ አስታወቁ፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስልጤ ዞን ሁለት ወረዳዎች እና በማረቆ ልዩ ወረዳ አንድ ቀበሌ ውስጥ በተከሠተ የጎርፍ አደጋ፣ ከስድስት ሺሕ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን፣ ተጎጂዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ አስታወቁ፡፡
በስልጤ ዞን ከስድስት ሺሕ በላይ ሰዎች በጎርፍ መፈናቀላቸው ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:54 0:00

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስልጤ ዞን ሁለት ወረዳዎች እና በማረቆ ልዩ ወረዳ አንድ ቀበሌ ውስጥ በተከሠተ የጎርፍ አደጋ፣ ከስድስት ሺሕ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን፣ ተጎጂዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ አስታወቁ፡፡

በዞኑ በስልጢ እና በምሥራቅ ስልጢ ወረዳዎች የተከሠተው የጎርፍ አደጋ መንሥኤ፣ በሁለቱ ወረዳዎች ከስድስት በላይ ቀበሌዎች ሰሞኑን የጣለውን ከባድ ዝናም ተከትሎ፣ ለመስኖ አገልግሎት ተብሎ በማረቆ ልዩ ወረዳ የተገነባ ኢንደሾ ልንጫ የተሰኘ ግድብ “በከፍተኛ ደለል መሞላቱ ነው” ሲሉም ነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡

በስልጢ ወረዳ የጎፍላላ ቀበሌ ነዋሪ መኾናቸውን የገለጹት አርሶ አደር ወርቅቾ ሱሩር፣ በጎርፍ አደጋው ከስምንት ልጆቻቸው ጋራ መፈናቀላቸውን ገልጸው፣ ከ650 በላይ አባዎራዎችም በአንድ ትምህርት ቤት መጠለላቸውን ተናግረዋል፡፡

በርካታ ሰዎች የተፈናቀሉባቸው ቀበሌዎች ጎፍለላ፣ አሹቴ፣ ሰዳጎራ፣ ምሥራቅ እየቆጬ፣ ምዕራብ እየቆጬ እና ባሎ ቀሪሶ እንደኾኑም አርሶ አደር ወርቅቾ ጠቁመዋል።

አቶ አሕመድ ሾሞሎ የተባሉ የወረዳው ነዋሪ በበኩላቸው፣ የጎርፍ አደጋው መንሥኤ፣ በማረቆ ልዩ ወረዳ እና በስልጢ ወረዳ አዋሳኝ ቦታ ከዓመታት በፊት የተገነባ ግድብ ነው፤ ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከዚኽ በፊት፣ በከፍተኛ ስፍራዎች ከባድ ዝናም በሚጥልበት ወቅት የሚፈጠረው ጎርፍ፣ የማረቆ ልዩ ወረዳን በማቋረጥ ወደ ዝዋይ ሐይቅ ይፈስ እንደነበረ ነው አቶ አሕመድ የተናገሩት፡፡

በሁለቱ ወረዳዎች የተከሠተው የጎርፍ አደጋ፣ አርሶ አደሮችን ከማፈናቀሉ በተጨማሪ፣ በ1ሺሕ200 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ የበቆሎ፣ የስንዴ፣ የማንጎ፣ የፓፓያ እና የቡና ምርት ሙሉ በሙሉ ማውደሙንም አቶ አሕመድ ገልጸዋል፡፡

የስምንት ልጆች አባት የኾኑት አቶ ወርቅቾ፣ ተፈናቃዮቹ ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው፣ ከምንም በላይ ግን ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈለግላቸው ጠይቀዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ማዕርጉ ማቴዎስ፣ በአደጋው ከአንድ ሺሕ በላይ አባወራዎች መፈናቀላቸውን አረጋግጠው፣ ለተፈናቀሉ ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ እየቀረበ ነው፤ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አደጋው ጉዳት ማድረስ የጀመረው ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ መኾኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ ከፌዴራል መንግሥት እና ከክልሉ አስተዳደር የተወጣጡ ባለሞያዎችም የአደጋውን መንሥኤ በማጥናት ላይ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት፣ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ባወጣው የማስጠንቀቂያ መግለጫ፣ ለተከታዮቹ 11 ቀናት ተደጋጋሚነት ያለው ከባድ ዝናም እንደሚጥል ጠቁሞ፣ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት የማስከተል ዓቅም ስለሚኖረው የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቦ ነበር፡፡

ይህንኑ የተቋሙን ማሳሰቢያ የጠቀሱት አቶ ማዕርጉ፣ በክልሉ በጉራጌ፣ በስልጤ እና በየም ዞኖች የጎርፍ እና የናዳ፤ በሐዲያ እና በሀላባ ዞኖች ደግሞ የመሬት መሠንጠቅ እና የጎርፍ፤ እንዲሁም በከምባታ የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋዎች ሊከሠት እንደሚችል ጠቁመዋል። ኅብረተሰቡ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል።

በተለይም፣ ከመሬት መንሸራተት አደጋዎች ጋራ በተያያዘ፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት ያሰፈሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ "በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በመሬት መንሸራተት ወገኖቻችን በመጎዳታቸው የተሰማኝን ኀዘን ለመግለጽ እወዳለኹ፤" ብለዋል። የሚመለከታቸው አካላት ለተጎጂዎች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ መመሪያ መሰጠቱንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው አስታውቀዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG