ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ሦስት ቢሊዮን ዶላር ብድር አግኝታም በዶላር እጥረት የተቸገረችው ግብጽ የአገር ሃብቷን ለዓረብ አገራት ለመሸጥ ወስናለች፡፡
ባለሙያዎች እንደሚሉት ሽያጩ ሁለቱንም ወገኖች አሸናፊ የሚያደርግ ቢሆንም፣ ግብጽ አንዳንድ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ እንድታደርግ ይጠበቅባታል፡፡
የሃብት ሽያጩ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በመጪው አራት ዓመታት 17 ቢሊዮን ዶላር እጥረት ያሳያል ያለውን ክፍተት እንደሚሞላ ካይሮ ተስፋ ታደርጋለች፡፡
ለኩዌት፣ ካጣር፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ አጋጣሚው በነዳጅ ብቻ የታጠረውን ኢኮኖሚያቸውን ወደ ሌሎች ሃብቶች ለማስፋፋት ይጠቅማቸዋል ተብሏል፡፡ በግብጽ መሬትና የመንግሥት ኩባንያዎች ውስጥ ሽርክና በመያዝ ዓረቦቹ ሃብታቸውን እንዲያሰፉ ያስችላቸዋል ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ አል_ሲሲ ዋጋው እንዲቀንስ የተደረገው የግብጽ መገበያያ ገንዘብ ለዓረብ አገራቱ ጥሩ አጋጣሚ ነው ተብሏል፡፡
አገራቱ ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ለግብጽ ቼክ መላኩን አቁመው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲደረና ግልጽነት እንዲኖር ጠይቀዋል፡፡