በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ ውስጥ ህይወታቸው ያለፈው የካርተር ማዕከል ታዛቢ


ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ
ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ በተካሄደበት ባለፈው ሰኞ የምርጫ ታዛቢ የነበሩት አሜሪካዊ ህልፈት የበቁበት በተፈጥሯዊ ምክንያት መሆኑን ምርመራውን ያደረገው የአዲስ አበባው ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ማረጋገጡን የፈዴራል ፖሊስ አስታወቀ።

የዩናይትድ ስቴትሱ የካርተር ማዕከል ወደኢትዮጵያ በተጓዘው የማዕከሉ ቡድን አባሉ ድንገተኛ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል።

በኢትዮጵያ የተካሄደውን ምርጫ ለመከታተል ከካርተር ማዕከል የተጓዙት አሜሪካዊ ጃን ማርሽ አዲስ አበባ ውስጥ ባረፉበት የራዲሰን ብሉ ሆቴል ክፍል ውስጥ ህይወታቸው አልፎ ሰኞ ጠዋት በሆቴሉ የጽዳት ሰራተኛ መገኘቱን ፖሊስ ማስታወቁ ይታውሳል።

የካርተር ማዕከል ትናንት ባወጣው መግለጫው በኢትዮጵያ በማኅበራዊ መገናኛ የሚዘዋወሩ ንግግሮች ክትትል መርሃ ግብሩን በኮንትራት ቅጥር በኃላፊነት ይመሩ የነበሩት ባልደረባው በድንገት ህይወታቸው ማለፉን እንዳረጋገጠ ገልጿል።

ግለሰቡ በምስራቅ አፍሪካ እና በዓለም ዙሪያም ጠንካራ ለሰብዓዊ መብቶች ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ ተሙዋጋች እንደነበሩ እና ባለፉት ዓመታትም በበርካታ ትላልቅ መርሃ ግብሮች ተመድበው የሰሩ መሆናቸውን የካርተር ማዕከል አውስቶላቸዋል።

እአአ ከ2005 እስከ 2008 በኢትዮጵያ ምርጫዎች እና ዲሞክራሲያዊ ውይይቶች ዙሪያ ድጋፍ ለመስጠት ማዕከሉ ያደረጋቸውን ጥረቶች በኃላፊነት የመሩት ጆን ማርሽ እንደነበሩ ገልጿል። በማስከተልም በ2008 እና በ2009 የጋናን ምርጫ ታዛቢ ቡድኖችን በመምራት እንደረዱ ተናግሮላቸዋል።

ሟቹ ለማኅበራዊ ፍትህ እና ለሙያቸው ባላቸው ፍቅር እና በመልካም ባህሪያቸው በማዕከሉ በጉዋደኞቻቸው እና በባልደረቦቻቸው የሚወደዱ ነበሩ ያለው መግለጫው ለቤተሰባቸው ልባዊ ሃዘናችንን እንገልጻለን ብሏል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስን ስለካርተር ማዕከል የምርጫ ታዛቢ ሞት እንዲሁም በኢትዮጵያ ስለተካሄደው ምርጫ ቪኦኤ አስተያየታቸውን ጠይቆ ነበር። የዩናይትድ ስቴትስ ዜጋ አዲስ አበባ ውስጥ ህይወቱ ማለፉን ማረጋገጣችንን ከሃዘን ጋር እናስታውቃለን። ሆኖም ለቤተሰባቸው ክብር ስንል ባሁኑ ሰዓት ከዚያ በላይ በዝርዝር መናገር አንችልም ሲሉ መልሰዋል።

ስድስተኛውን ብሄራዊ ምርጫ በተመለከተ ሲናገሩም

"እኛ የምናውቀው ምርጫው በሀገሪቱ እየጨመሩ ላሉት ግጭቶች መፍትሄ እንደማያመጣ ነው። ምርጫው ውይይት፥ ትብብር እና ሰጥቶ መቀበል ባለው መልኩ ሰፋ ብሎ የሚከናወን የፖለቲካ ሂደት አካል መሆን አለበት። ዲሞክራሲን የሚያጠናክር ለብሄረሰባዊ እና ማኅበረሰባዊ ግጭቶች መፍትሄ በማምጣት የሚያግዝ አሳታፊ የፖለቲካ ንግግር እንዲካሄድ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁርጠኛ እንዲሆን እንማጸናለን" ሲሉም ኔድ ፕራይስ አክለዋል።

XS
SM
MD
LG