በደቡብ ምሥራቅ ናይጄሪያ በመኪና አጀብ ላይ በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት አራት የፀጥታ ጥበቃ አባላት መገደላቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
አንድ የቀድሞ የመንግሥት ባለሥልጣንን ኢላማ አድርጎ የነበረ ጥቃት ነው ተብሏል።
ኢሞ ስቴት በተባለችው የናይጄሪያ ክፍል የቀድሞ የአካባቢው ገዢ የነበሩትን ኢኬዲ ኦሃኪም ይዞ በነበረው የመኪና አጀብ ላይ በተወረወረ ቦምብ ሦስት ፖሊሶችና አንድ የፓራሚሊታሪ አባል መገደላቸውን የፖሊስ ኮሚሽነር ሞሃመድ ባርዴ አስታውቀዋል።
“ኦሃኪም ላይ የደፈጣ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። ግን በዘዴ አምልጠዋል። በሌላ መኪና የነበሩ አራቱ ጸጥታ አስከባሪዎች ተገድለዋል። ጥቃቱ በግጭት በታመሰው የደቡብ ምሥራቅ ናይጄሪያ ክፍል መንግሥት ሰላም ለማስፈን በሚያደርገው ጥረት ላይ እንቅፋት ይሆናል” ብለዋል ኮሚሽነሩ።
በደቡብ ምሥራቅ ናይጄሪያ ክፍል ባለፉት ዓመታት ሁከት እየጨመረ መጥቷል። ይህም በአብዛኛው ተገንጥለው ነጻ አገር ለመመስረት የሚጥሩ ቡድኖች በሚያደርሱት ጥቃት ምክንያት ነው ተብሏል።
ተገንጣዮች የተባሉትና እራሳቸውን ‘የቢያፍራ ነባር ሕዝቦች’ ብለው የሚጠሩት ቡድኖች ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ በሚጠየቅበት በዚህ ወቅት ጥቃታቸውን እየጨመሩ መምጣታቸውን የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።
ጥቃቶቹ በአብዛኛው በደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል ባለሥልጣናትንና ፀጥታ ጠባቂዎችን ኢላማ ያደረጉ መሆኑን የግጭት ተንታኞች ይናገራሉ።
ጥቃት ፈፃሚዎቹን ለመያዝ አሰሳ መጀመሩን ባለሥልጣናት ጠቁመዋል።
በአገሪቱ በሚቀጥለው ወር በሚደረገው ምርጫ ምክንያትም የፀጥታ ሁኔታው ይበልጥ እንዳይበላሽ የአካባቢው ነዋሪዎች ይሰጋሉ።
ባለፈው መስከረም አናምብራ በተባለ ግዛት በአንድ የፓርላማ አባል ላይ በተፈጸመ የደፈጣ ጥቃት አራት ፖሊሶች ተገድለዋል።
ከዛ ጥቃት በኋላ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሞሃማዱ ቡሃሪ በሁከት የታመሰው አካባቢ ጉዳይ እጅግ እንዳሳሰባቸው ተናግረው ነበር።