በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ የጦር መሣሪያዎችን በማቅረብ በዩናይትድ ስቴትስ ተከሠሠች


ፎቶ ፋይል፦ አምባሳደር ሩበን ብሪጌቲ
ፎቶ ፋይል፦ አምባሳደር ሩበን ብሪጌቲ

በደቡብ አፍሪካ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሩበን ብሪጌቲ፣ ደቡብ አፍሪካ፥ ሩሲያ በዩክሬን ለምታካሒደው ጦርነት፣ የጦር መሣሪያዎችንና ጥይቶችን አቅርባለች፤ ሲሉ ከሠሡ፡፡

ደቡብ አፍሪካ፣ መሣሪያውን በድብቅ ያቀበለችው፣ ባለፈው ታኅሣሥ ወር፣ ኬፕ ታውን ከተማ አቅራቢያ ከሚገኘው የባሕር ኃይል ጦር ሠፈር፣ ማዕቀብ በተጣለበት የጭነት መርከብ ድርጅት አማካይነት እንደኾነ አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

አምባሳደሩ፣ ጉዳዩን በጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ከማድረጋቸው በፊት፣ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራሞፎሳ፣ “ሌዲ አር” የተባለችው የሩሲያ መርከብ፣ ወደ አገራቸው ዋና የባሕር ኃይል ጦር ሠፈር የመጣችበት ምክንያት፣ በዩናይትድ ስቴትስ የመረጃ ድርጅት እገዛ እየተመረመረ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

አምባሳደር ብሪጌቲ፥ እ.ኤ.አ. ከታኅሣሥ 6 እስከ 8 ባሉት ቀናት፣ ሳይመን ታውን በተባለው የባሕር ኃይል ጦር ሠፈር፣ “ሌዲ አር” በተባለችው መርከብ ላይ፣ ወታደራዊ የጦር መሣሪያዎች መጫናቸውንና ወደ ሩሲያ መጓጓዛቸውን፣ ዩናይትድ ስቴትስ ርግጠኛ ናት፤ ብለዋል፡፡

የደቡብ አፍሪካ የጦር መሳሪያዎች ቁጥጥር ኮሚቴ ሰብሳቢ ዛሬ 702 ለተባለው ራዲዮ ጣቢያ በሰጡት አስተያየት “ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ እንዲላክ አልፈቀደችም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ለሩሲያው የተጫነ የጦር መሳሪያ ካለ ግን ሕገ ወጥ እና ተገቢ እንዳልኾነ መናገራቸውን የራዲዮ ፕሮግራም አዘጋጁ በትዊተር ገፁ ላይ አስፍሯል።

“ሩሲያውያንን ማስታጠቅ እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ በመኾኑም፣ ጉዳዩ እልባት እንደተሰጠው አድርገን አንወስደውም፤” በማለት አምባሳደር ብሪጌቲ መናገራቸው፣ በብዙዎቹ የደቡብ አፍሪካ ዜና አውታሮች መጠቀሱን አሶሽየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

ደቡብ አፍሪካ፣ ወታደራዊ ርዳታውን ለሩሲያ መስጠቷ ከተረጋገጠ፣ በዩናይትድ ስቴትስ እና በአፍሪካ ቁልፍ አጋሯ በኾነችው ደቡብ አፍሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዳያሻክረው ስጋት እንደፈጠረ በዘገባው ተመልክቷል፡፡

ምንም እንኳ ደቡብ አፍሪካ፣ በዩክሬኑ ጦርነት ገለልተኛ አቋም ብትይዝም፣ የባይደን አስተዳደር፣ በአፍሪካ እያደገ የመጣውን የሩሲያ እና የቻይና ተጽእኖ ለመቋቋም፣ ቁልፍ መከላከያ እንደምትኾን ተስፋ አድርጎ እንደነበርም ተገልጿል፡፡

የራማፎሳ ጽ/ቤት፣ ትላንት ኀሙስ አመሻሹ ላይ በአወጣው መግለጫ፣ በሌዲ አር ላይ የጦር መሣሪያ ተጭኗል ስለተባለው ውንጀላ፣ “ምንም ማረጋገጫ የለም” ቢልም፣ አሶሽየትድ ፕሬስ ግን፣ መርከቢቱ፥ ባለፈው ዓመት ለሩሲያ መንግሥት ወታደራዊ መሣሪያዎችን ያጓጉዛል፤ በሚል በዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ ከተጣለበት ድርጅት ጋራ ግንኙነት እንዳላት አረጋጫለኹ፤ ብሏል፡፡

XS
SM
MD
LG