“ኢትዮጵያ በየጊዜው ከፍተኛ መጠን ያለው እርዳታ ከካናዳ መንግስትና ሕዝብ ታገኛለች። በቅድሚያ ያ እርዳታ በረሃብ አለንጋ ለሚገረፉት ለእነኚያ ለታሰበላቸው ተረጂዎች መድረሱንና የሰዎች መብት መጠበቁን ማረጋገጥ እንሻለን። በእርግጥ የምናየው የሰብዓዊ መብት ረገጣ ግን በተዘዋዋሪም ቢሆን ያን ዓይነት አመኔታ እንድናሳድር የሚያግዝ አይደለም።” ለኢትዮጵያው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ግልጽ ደብዳቤ የጻፉት የካናዳ ፓርላማ አባል አሌክስ ናዳል።
ድርጊቱ ከተፈጸመ ቀናት ቢያስቆጥርም አሁንም እያነጋገረ ነው። ከጉዳዩ ጋር የሚዛመዱ ሌሎች አዝማሚያዎችን ጨምሮም የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ሰሞኑን በሰፊው ለመዳሰስ የበቃ ርዕስ ነው።
የንግግር ነጻነት በማንም የማይቸር በማንም የማይደፈር ሰብዓዊ መብት ነው፤ ሲሉ ይንደረደራሉ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የቴዲ አፍሮን የሙዚቃ ኮንሰርት መሰረዝ ተንተርሶ ሰሞኑን ለኢትዮጵያው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ግልጽ ደብዳቤ የጻፉ አንድ የካናዳ ፓርላማ አባል ለአሜሪካ ድምጽ በሰጡት አስተያየት።
ለአዲስ ዓመት መግቢያ አዲስ አበባ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረውን የድምጻዊ ቴዲ አፍሮ የሙዚቃ አልበም ምረቃ በባለ ስልጣናት መሠረዝ ዜና አስመልክቶ ደብዳቤውን የጻፉት የካናዳው ፓርላማ አባል የመንግስቱ እርምጃ የዜጎችን መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት የሚጋፋ በመሆኑ መቀልበስ አለበት ነው፤ የሚሉት።
አገራቸው ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን እርዳታ በእርግጥ ለተጎጂው የሚደርስ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚሹ መሆናቸውን ጨምረው ገልጠዋል።
“ዓለም ለኢትዮጵያዊው የሙዚቃ ኮከብ የአድናቆት ፍቅር ቢቸረውም የገዛ አገሩ መንግስት ግን ግድ የለውም” ይላል በመግቢያው የተጠቀሰው የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ከትላንት በስቲያ እሁድ በዓለም አቀፍ አምዱ ያስነበበው ጽሁፍ ርዕስ በግርፉ ወደ አማርኛ ሲመለስ።
የቴዲ ጉዳይ የዋሽንግተን ፖስት’ን ብቻ ሳይሆን በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሰሞን ሊካሄድ ታስቦ የተሰረዘው ዝግጅቱ የሌሎችንም ቀልብ ስቧል።
አሌክስ ናዳል ለፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በጻፉት በዚህ ግልጽ ደብዳቤያቸው ሙዚቃና ሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎች የአገርን አያያዝ እና ሁኔታ ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው፤ ይላሉ።
እነኚህን መብቶችና ርዕሰ ጉዳዮች አስመልክቶቶ በአገራቸው ፓርላማም ሆነ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በግልጽ በመናገር የሚታወቁ መሆናቸውን የተናገሩት የካናዳው ፓርላማ አባል፤ በተለይም ደግሞ ይህን መሰል የመብት ጥሰቶች ከግብር ከፋዩ ካናዳዊ በሚሰበሰብ ገንዘብ በሚረዱ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የካናዳ ወዳጅ አገሮች ውስጥ ሲፈጸም እነኚህን ጥያቄዎች በቀጥታ ለማንሳት የሚገፋፉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ሚ/ር ነዳል አክለውም፤ “አገርና መንግስት ለሕዝቡ፤ ለዜጎች ፍላጎት እንጂ ለመንግስቱ ፍቃድና ፍላጎት አይደለም የሚቆሙት። እነኚህ መብቶች ባልተከበሩበት ዲሞክራሲ ብሎ ነገር የለም።” ይላሉ።
ግልጽ ደብዳቤውን ከጻፉላቸው ከኢትዮጵያው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ቢሮ የተሰጠ ምላሽ እስከ አሁን ያለመስማታቸውን ሚር ነዳል ተናግረዋል።
ከግብር ከፋዩ በሚሰበሰብ ገንዘብ የሚረዱ አገሮች አገርዎ ካናዳ ‘ቆማላቸዋለች’ ላሏቸው እሴቶች መዋላቸውን ማረጋገጫና ማስጠበቂያ አንዳች በሥራ ላይ የዋለ ሥርዓት፤ ወይም አሠራር አላችሁ ይሆን? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ሚር ነዳል ሲመልሱ፤ አገራቸው በቀጥታ ለአገሮች የምትለግሰውም ሆነ በተዘዋዋሪ በተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት አማካኝነት የምንሰጠው እርዳታ ለታለመበት መድረሱን ለማረጋገጥ እንሻለን፤ ብለዋል።
የፕሬዝዳንት ተሾመን ጽ/ቤት ምላሽ ለማካተት ያደረግንው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። ቃል የተገባለትን የቴዲ አፍሮን የራሱን ድምጽ ጨምረን ሁሉንም እንዳገኘን እናቀርባለን።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ከፍተው ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ