በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ካናዳ ከፍተኛ የሕንድ ዲፕሎማትን አባረረች


የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ

►ህንድ የቀረበባትን ውንጀላ መሰረተ ቢስ ነው ብላለች

ካናዳ፣ አንድ የሕንድ ከፍተኛ ዲፕሎማትን፣ ትላንት ሰኞ ከአገሯ አባራለች። ዲፕሎማቱ የተባረሩት፣ በካናዳ ነዋሪ በነበሩትና ‘ሲክ' በተሰኘ የሕንድ ማኅበረሰብ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አራማጅ ላይ በተፈጸመው ግድያ፣ የሕንድ መንግሥት እጁ እንዳለበት ተኣማኒ ማስረጃ መኖሩን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ካስታወቁ በኋላ ነው።

ትሩዶ ለአገሪቱ ፓርላማ በሰጡት ገለጻ፣ የካናዳ የደኅንነት ተቋማት፣ የ‘ሲክ’ ማኅበረሰብ መሪ የነበሩት ሃርዲፕ ሲንግ ኒጃር፣ ባለፈው ሰኔ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ክፍለ ግዛት ‘ሰሪ’ ከተማ ውስጥ ከሚገኘው የማኅበረሰቡ የባህል ማዕከል ደጃፍ ላይ፣ በተተኮሰባቸው ጥይት የተገደሉበትን ወንጀል ጉዳይ እንደመረመሩ አስረድተዋል።

ትሩዶ አያይዘውም፣ ባለፈው ሳምንት ከተካሔደው የኻያዎቹ የዓለም ቱጃር ሀገራት(ቡድን-20) ጉባኤ ትይዩ፣ ከሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋራ፣ ስለ ግድያ ወንጀሉ ጉዳይ አንሥተው መነጋገራቸውንና እንዲህ ባለ ጉዳይ የሕንድ መንግሥት ተሳትፎ ተቀባይነት እንደሌለው ለሞዲ እንደነገሯቸው ለፓርላማው ገልጸዋል። በተጨማሪም ሕንድ፣ በምርመራ ሒደቱ እንድትተባበር ሞዲን እንደጠየቋቸው ተናግረዋል።

ህንድ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር የህንድ መንግሥት ከካናዳዊው የሲክ መሪ መገደል ቁርኝት አላት ያሉትን ውንጀላ ውድቅ አድርጋለች። የኒውዴልሂ መግለጫ የተሰማው ካናዳ የሕንዱን ዲፕሎማት ከሃገር ካባረረች ሰዓታት በኋላ ነው። የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አክሎም ካናዳ ለሲክ "አክራሪዎች" አስተማማኝ መሸሸጊያ ሆናለች” የሚለውን የኒውዴልሂን ስጋት አስረግጧል።

የካናዳዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜላኒ ጆሊ በበኩላቸው፣ በካናዳ የነበሩት የሕንድ የደኅንነት ጉዳዮች ሓላፊ፣ በዚኹ ምክንያት እንደተባረሩ ተናግረዋል።

ጆሊ አክለውም፣ “ድርጊቱ ትክክል ኾኖ ከተገኘ፣ ሉዓላዊነታችንንና ሀገራት እርስ በርስ የሚግባቡባቸውን መሠረታዊ ደንቦች በእጅጉ የጣሰ ነው፤” ብለውታል።

የዲፕሎማቱ ከሀገር የመባረር ዜና የተሰማው፣ በካናዳ እና በሕንድ መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት ውስጥ በገባበት ወቅት ነው፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚደረጉ የንግድ ድርድሮች እንደተስጓጎሉና ካናዳ ወደ ሕንድ ለመላክ ያቀደችውን የንግድ ተልዕኮ እንደሰረዘች ታውቋል።

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ አስተያየት ለማግኘት፣ ኦታዋ ለሚገኘው የሕንድ ኤምባሲ ላቀረበው ጥያቄ፣ ለጊዜው ምላሽ ያለማግኘቱን፣ የአሶሺዬትድ ፕሬስ ዘገባ አክሎ አመልክቷል።

ሟቹ ኒጃር፣ ካሊስታን በመባል የሚታወቅ ከሕንድ ነፃ ግዛት ለመመሥረት ለተያዘው አቋም ጠንካራ ድጋፍ በመስጠት ይታወቃሉ።

አብዛኛው የ‘ሲክ’ ማኅበረሰብ አባላት፣ በሰሜናዊ ሕንዷ ፑንጃብ ግዛት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የሚያራምዱት የሲክሂዝም ሃይማኖትም፣ ባሉት 21 ሚሊዮን ተከታዮች ብዛት በሕንድ በትልቅነቱ አራተኛው ሃይማኖት ነው።

/ዘገባውን ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል/

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG