የገባበት ሳይታወቅ የሰነበተው ታዋቂ ካሜሮናዊ የራዲዮ ጋዜጠኛ ሞቶ መገኘቱን ይሰራበት የነበረው ጣቢያ እና ፖሊስ ትናንት አስታወቁ። ዜናው የተሰማው አንድ የመገናኛ ብዙኃን መብት ተሟጋች ድርጅት “የተጠለፈው ሰው ተገድሏል” ካለ በኋላ ነው።
ማርቲኔዝ ዞጎ ያውንዴ የሚገኘው አምፕሊቱድ ኤፍ የተባለው የግል ራዲዮ ጣቢያ መራሄ ድሬክተር እና የታዋቂው “ኢምቦቲላጅ” ወይም “አጣብቂኝ” የተሰኘው ዕለታዊ ፕሮግራም አዘጋጅ እና አቅራቢ ነበር።
የ51 ዓመቱ አንጋፋ ጋዜጠኛ ታዋቂ ግለሰቦችን ሳያመነታ በስም እየጠራ
በየጊዜው በሙስና ላይ ያተኮሩ ጉዳዮችን እያነሳ በፕሮግራሙ ያስተናግድ ነበር። ካለፈው ማክሰኞ አንስቶ ግን የገባበት ሳይታወቅ በመቅረቱ እየተፈለገ ነበር።
የዞጎን ሞት ለኤኤፍፒ ያረጋገጡት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የፖሊስ ምንጭ መሆናቸውን የዜና አገልግሎቱ ጨምሮ ዘግቧል።