ዋሺንግተን ዲሲ —
የካሜሮን ፕሬዚዳንት ፖል ቢያ በቅርቡ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸው ፀንቶላቸው ለሰባተኛ አከታታይ የሥልጣን ዘመን ሊቀጥሉ ነው።
ራሳቸው ፕሬዚዳንቱ የሰየሙት ህገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ተቃዋሚዎች የምርጫውን ውጤት በተመለከተ ያቀረቡባቸውን የህግ አቤቱታዎች በዛሬው ዕለት ውድቅ አድርጓል።
የፕሬዚዳንቱ ተቃዋሚዎች በስፋት መራጮችን ማስፈራራት እና ድምፅ ማጭበርበር የመሳሰሉ ድርጊቶች ተፈፅመዋል በማለት የድምፅ ቆጠራውን እንደማይቀበሉ ማስታወቃቸው ይታወሳል።
የተቃዋሚዎች ሰልፎችን በሙሉ በተከለከሉበትና በሀገሪቱ ዙሪያ ያሉ ከተሞች በወታደር ጥበቃ ሥር በዋሉበት ድባብ በተካሄደው ምርጫ ፕሬዚዳንቱ ሰባ አንድ ከመቶ ተቀናቃኛቸው ሞሪስ ካንቶ ደግሞ አሥራ አራት ከመቶውን ድምፅ አግኝተዋል።
እ ኤ አ ከ1982 አንስተው ሥልጣን ላይ የሚገኙት የሰማኒያ አምስት ዓመቱ ፖል ቢያ ከዓለም በዕድሜ የገፉ መሪዎች አንዱ ናቸው።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ