ካሊፎርኒያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ያለው ቀዝቃዛ አየር ፀባይና አነስተኛ ሙቀት፣ ባለፈው እሑድ የተነሳውን ሰደድ እሳት ለማጥፋት ለሚጣጣሩ የአሳት አደጋ ሠራተኞች መልካም አጋጣሚ መፍጠሩ ተገለፀ።
የካሊፎርኒያ የደንና የእሳት አደጋ ጥበቃ መከላከያ ሚኒስቴር በሰጠው ማስጠንቀቂያ፣ ነፋሻና ቀዝቃዛ አየር ፈተና ሊደቅን እንደሚችል አመልክቶ፣ ትናንት ማክሰኞ ማምሻው ላይ እሳቱ ከ46,500 ሄክታር በላይ ማውደሙንም ገልጧል።
ዛሬ ረቡዕ ባለሥልጣናት በሰጡት መግለጫ፣ 17 ሰዎች መሞታቸውንና ወደ 1ሺህ 5መቶ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማት መቃጠላቸውን አስታውቀዋል።
በርካታ የወይን ፋብሪካዎች ያሉባቸውና የቱሪስት መስህብ የሆኑት የናፓ እና የሰኖማ አውራጃዎች፣ በቃጠሎው ከተጎዱት ክልሎች መካከል ናቸው። ጠቅላላ በክፍለ ሀገሩ፣ በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የተፈናቀሉ ሲሆን፣ ብዙዎችም ወደየመጠለያ ጣቢያዎች መላካቸው ታውቋል።
የአውራጃው ገዢ ጄሪ ቤተሮውን በስምንት አውራጃዎች የአስቸኳይ ጊዜ አውጀው፣ ፌዴራል መንግሥቱም አጣዳፊ ምላሽ በመስጠቱ አመስግነዋል። ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት ማክሰኞ የፌዴራሉን እርዳታ አፅድቀዋል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ